Sunday, April 5, 2009

ነጻነት ምንድነው? (መጀመሪያ የሞከርኩት ግጥም)

""ነጻነት ምንድነው ?""

ድፍን ቢሆንበት ትርጉሙ ባይገባው
ይጠይቅ ጀመረ ""ነጻነት ምንድን ነው ?""
"'ነጻነት የማን ነው ?""
በስተምዕራብ ያሉት ፊደል የቆጠሩት
..... ሎጂክ ያነበቡት
ትርጉሙን ሊያብራሩ ተረባረቡበት

ሩሶ እንደገባው እንደተረጎመው
የሰው ልጂ ነጻነት ገና ከሙጣው ነው
ሲወለድ ያገኘው አብሮት የመጣ ነው
ከዚያ በኁላ ነው ቀማኛ ያገኘው
እስር ቤት ሳይገባ ሰው የታሰረው
ሩሶም የሚያየው ግለሰብን ሳይሆን
ሕብረተሰብን ነው
ይሁን ትርጉም አለው

ለየቅል ቢሆንም ማርክስም የሚለው
የሩሶ ቢጤ ነው
ዙሪያውን የሚያየው የታሰረ ሰው ነው
ሰንሰለቱን ያየው አንድ መደብ ላይ ነው
እሱም ሀሰት የለው አሁንም ልክ ነው
ፍዳውን የሚያው አፈር የሚበላው
ከወደታች ያለው አብላጫ የሆነው
ማርክስም የሚለው የሰው ነጻነት ነው
ያንን ገለባብጦ ሰንሰለቱን ፈቶ ሳይጫን ሲኖር ነው
ይሔም ትርጉም አለው

ሚል ደሞ የሚለው የሰው ነጻነት ነው
ሌሎችን ሳይነኩ እንዳሻ መሆን ነው
ብዙሀኑን ትቶ ነጠላ ነው ያየው
ምን አይነት ሎጂክ ነው ?

ሌሎችን ረስቶ
አብሮነትን ገፍቶ
ሰለጠነ መስሎት ...
ሲሆን አንቶ ፈንቶ
በግሩ ሲጠቀጥቅ ያብሮነት እሴቱን
አልነካም ሊባል ነው የህብረተሰቡን
ምን አይነት ሎጂክ ነው ሚል የደረደረው

ስራስ ቦታ ቢሆን ምኑን ተጠቀመው
በየፋብሪካው ውስጥ አሩን ለሚበላው
ጣቱን ለሚያጣበት ጎደሉ ላረገው
ነጻነት ምኑ ነው ከምንስ አዳነው
በመንግስት ፋንታ የቱጃር ተወካይ
...ቁም ስቅሉን ሲያሳየው
ፍጠን እንጂ "ሱቹፒድ ' ሲለው
ልብሱንም ቀይሮ ጺምህን ላጭ ሲለው
ፍሪደም የቱ ነው

ግራ የተጋባው
'ስትሬስ ' ያፈሰው
'ሊቭ ሚ አሎን ' እያለ ብቻውን የሆነው
እሱ ነው ነፃ ሰው ?
ባያውቀው ነው እንጂ እንዲያውም ባሪያ ነው
ግማሹን ነጻነት ለቀጣሪው ሰቶ
የተረፈውንም ከሱስ ጋር አጣብቶ
በስተመጨረሻ ራሱን ረስቶ
ተፈጥሮውን ስቶ ሲሆን አንቶ ፈንቶ
አሁንም ነጻ ነው
ሲናገር ስንሰማው
ምን አይነት ቋንቋ ነው ?!
እጁን ካልታሰረ ; እስር ቤት ካልገባ
ነጻ ነው ማለት ነው
ምን ድንፈፍነት ነው
አትንኩኝ ስላለ ነጻ ነው ማለት ነው ?
እስኪ በደንብ አስሉት
ትርጉሙን ፈትሹት
አትንኩኝ የሚለው
በማን ነው ያመጸው
...ጉንጩን ብልጥጥ አርጎ ጌቶቹ ጋር ስቆ
ሕዝቡን ሲያኮርፍ ነው ?
እሱ የሚነቃው ቤተሰቡ ላይ ነው
አትንኩኝ የሚለው ለመሸራገጥ ነው
እሱ ነው ነጻ ሰው
ሚል የሚያሞግሰው
ሚልስ አስመሳይ ነው
አዛኝ ቅቤ አንጉአች ነው ::

ነገሩ ወዲህ ነው
እሱ የተየበው ለማደናገር ነው
ሰንሰለት ደብቆ ሰው እንዳያየው
እያስፈነጠዘ ሊያደነፍፈው ነው
ሰውም እንዳያብር
ከሌላው እንዳይመክር
እንደፈለክ ሲባል
ራሱን ከልሏል
.....ከሰው አይገናኝ
ማን ይደርስለታል
.....አብሮት እየኖረ
መች ይነጋገራል
ይሄ ነው ነጻ ሰው
ሚል የከተበለት የሚያሞጋግሰው ::

የፈረንጁን ዜማ
አበሻ ቢሰማ
መናገር ይቻላል እንደማይስማማ ::
አበሻስ ምናለ ""ነጻነት ምንድን ነው ?""
አበሻ ጨዋ ነው
አትንኩኝ የሚልው
ላገር ለመሞት ነው
የህብረተሰቡን ክብር ሊያስጠብቅ ነው
ዜማውም ሌላ ነው
ክንዴን ሳልንተራስ ምን አይነት ወንድ ነው
ባህር ከፍሎ መቶ እኛን የሚገዛው
ያ ነው ያወራጨው
አበሻ ወንድ ነው !!

ደግነትም ቢሆን አብሮት የሚኖር ነው
እግዜር እንዳረገው
ለሰው የሚሞት ነው ::

ማንነቱን ይዞ መገዛትን ጥሎ
ወደ መሬት ቀብሮ
ሀገር አስከብሮ
በተከበረ አገር እኛነትን ተክሎ
ተክሉ አንዳይጠወልግ ደብዛው እንዳይጠፋ
ሲያርም ሲኮተኩት ማታ አያንቀላፋ
.....ጧት አያንቀላፋ
የሴትም ወንድ አለው አብራ ስትለፋ
የኔ አምበሳ አያለች ውስጡን ስታፋፋ
ኑሮውንም ሲኖር ሆዱ ዱጭ ሳይል አንገቱን ሳይደፋ
የነጻነት ትርጉም በልቡ ታትሟል ሆኖ እንደማይጠፋ ::

ይሄን እንደማያውቅ
የሌባ አይነ ደረቅ
መንገድ ሰብሮ መጣ ነጻነት ሊያሳውቅ
"'ባርነት ምን ሲባል "'ብለው የታገሉት
በለሱ ቀንቷቸው ሕዝብ ላይ ጉብ ያሉት
አዲስ ትርጉም ይዘው ተለቃለቁበት ::

ከዚህ መልስ ጋሞ
ከዚያ መልስ ኦሮሞ
ከዚህ መልስ ትግሬ
ከዚያ መልስ አደሬ
ይኼ ነው ነጻነት
ሌቦቹ እንደሚሉት ::

በፊት ያደገውን በብረት ቆረጡት
ተክሉም ጉደኛ ነው የማይለወጥ
በቆረጡት ቁጥር ነው የሚያቆጠቁጥ
ይኼ ነው ነጻነት
ስንቱ የሞተለት ::

የምን "'ሊቭ ሚ አሎን ""
እንደማያቅ ጥቅሙን
በህብረት መኖርን
ለህብረት መኖርን ::

ያበሻ ግለሰብ እንዳይወጣጠር
አገር በሱ ቆዳ ስለማትቀበር
ጠንቅቆ ይያዘው የህብረቱን ነገር ::
እሱ ባገር ቆዳ መቀበሩን አይሳት
ያ የሆነው ታዲያ አትንኩን እያለ ሰው ስለሞተለት ::

ተቃዋሚም ይወቅ ይህንን እንዳይስት
በነጻነት ሂሳብ ሳይገባው አይኮትኩት
ድንፈፍ የሚያፈራ የነጻነት ፈሊጥ
የሕብረቱን ያጥብቅ
እንደዋዛ እንዳይደርቅ ::

አበሻ ተባርኮአል
"ነግ በኔ " ሲታደል
በብዙ ደርሶታል
ሀዘን ይካፈላል
ደስታ ይካፈላል
መጋራትን ያውቃል
ምን ቁርጥ አድርጎት እኔነት ይነግሳል
ሌላውስ ተረስቶ እሽክትር ይመታል
ሰው የሞተበትስ በእግሩ ይረገጣል ?!


አበሻ ጨዋ ነው !
አትንኩኝ የሚለው
ጥቃት ከተቃጣ
ባገር ከተመጣ
ያኔ አያቅም ጣጣ ::

ሲፈጥረው አበሻ ጥንቁቅ ነው
አበሻ ንቁ ነው
ወደ ውጭ ወቶ ጥራዝ የነጠቀው
""ፍሪደም "" እያለ ግራ እንዳያጋባው
ከድንፈፍነት ጋር ወስዶ እንዳያጣባው
የሕብረቱን ተክል ያን እንዳያስረሳው
ያንን ቅን አበሻ እንዳያሳስተው
አደራየ ይህ ነው ::

አበሻ ገብቶታል
ነጻነቱን ያውቃል
የሰረቀውንም በደንብ አርጎ አውቆታል
የጊዜ ጉዳይ ነው እጁ ያስገባዋል
ሌባም ይታሰራል
የሕብረቱም ተክል እንዳዲስ ያብባል ::

አንድ ነገር ልበል
ሀሳብ ለመጠቅለል
እኛ የወጣነው
ያንን እንዳንረሳው
ሰለጠንን መስሎን
እንዳንጥል አውጥተን !
በሞት የቀናውን የነጻነት ትርጉም
ያ ነው የሚስማማን !!

ስማርት ማለትም ትርጉሙ ወዲህ ነው
የብብት ሳይወድቅ የቆጡን ማውረድ ነው
የቆጡም ካልጣመ እዚያው መመለስ ነው
ፍሪደም የሚሉት ጥሩንባ ብቻ ነው
እሱ የሚጠቅመው ለቱጃሮቹ ነው
ሰው እንዳይባንን ለማደንፈፊያ ነውመስከረም 17, 2001 ዓመተ ምህረት

No comments:

Post a Comment

Blog Archive