Sunday, April 29, 2012

“የሀበሻ ጀብዱ”

ከተፃፈበት የቸክ ቋንቋ ርዕስ Habešská Odyssea “የሀበሻ ጀብዱ” በሚል የተተረጎመውን መጽሀፍ በተመስጦ አነበብኩት:: መጽሀፉን የጻፉት ቸኮዝሎቫኪያዊው (በድሮው) ብዙ ጊዜ እንደተለመደው “ታሪክን እና ማህበረሰብን እናጠናለን” በሚል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መዛግብትን በማስተርጎም እና ቃለ-መጠየቅ በማድረግ በየሚያሳትሟቸው መጻህፍቶቻቸው ስለ ኢትዮጵያ እንደሚዘባርቁት ሳይሆን ከዚህ በተለየ ምክንያት ፈታኝ በሆነ ሰዐት ኢትዮጵያ ተገኝተው በብዙ የጦር ውሎዎች እና ሌሎች ሁነቶች በአካል ተግኝተው ያዮትን ነው የጻፉት:: አልፎ አልፎ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከሚሰጡ በስተቀር ጸሀፊው ከትንተና እና ማብራሪያ ታቅበው የጦርነት ውሏቸውን እና ገጠመኖቻቸውን በጥሬ መረጃ መልክ አቅርበዋል:: ይሄ ማለት ለታሪክ ተመራማሪዎች በመረጃነት ለትንተናቸው እንደመነሻ የሚሆን እጂግ ጠቃሚ ስራ ነው ማለት ነው:: የታሪካዊ ምርምር አጻጻፍ ክህሎት የሌለውም ቢሆን ከታሪኩ ሊወስድ የሚችላቸው ጠቃሚ መረጃዎች አሉ::




ከኢትዮጵያዊነት እሴቶች ጋር በተያያዘ ሲንጸባረቅ የሚታይ ደግነት : የዋህነት: ፈሪሀ እግዚያብሄር እና እምነት : አልበገር ባይነት: እጂግ በጣም ጥልቅ የሆነ ከነብስ ጋር የተሳሰረ የሀገር ፍቅር: የአሸናፊነት ስነ ልቦና : ታዛዢነት : ታማኝነት : አንድነት: ከልክ ያለፈ ወኔ : ግፍና መከራ ችግር ቻይነት የመሳሰሉትን ስናይ በሌላ በኩል ደሞ ከነውር እና ከሀጢያት እኩል ይቆጠሩ የነበሩ ከኢትዮጵያዊነት እሴት ጋር አይን እና አፈር የሆኑ ነገሮችንም እናያለን:: ከክህደት እና ሀገር አሳልፎ ከመስጠትም በተጨማሪ ከጠላት ጎን ተሰልፎ በገንዘን ተቀጥሮ ኢትዮጵያን የወጋ አለ:: ስግብግብነት አለ:: ወራት ያስቆጠረ ረዢም መንገድ እና እንግልት ተቋቁሞ ህይወቱን ሊሰጥ ትግራይ መሬት የረገጠውን ከከምባታ ከሰላሌ ከሸዋ ከጎንደር እና ከሌላውም የመሀል ሀገር የመጣውን የኢትዮጵያን ሰራዊት ከጣሊያኖች ስንቅ እና ትጥቅ ድጋፍ ጠይቆ ተደራጂቶ የዘረፈ እና ኢትዮጵያን የወጋ ቡድንም አለ:: (ከታች ከነማጣቀሻ ገጹ በጨረፍታ እጠቁማለሁ:: )

የታየው ክህደት የሚያበሳጨውን ያህል ጸሀፊው ቅልጥ ባለ ጦር ሜዳ ላይ በባለ ጎራዴው የኢትዮጵያ ገበሬ እና እስካፍንጫው በታጠቀው የጣሊያን ሰራዊት መካከል በነበረው ግብ ግብ ባለጎራደው የኢትዮጵያ ገበሬ በደም ፍላት እየዘለለ የጣሊያኖቹን አንገት ሲመትር ያዮትን የጀግንነትና የወኔያምነትን ጥግ ያለ ምንም ቁትብነት ስዕላዊ በሆነ ሁኔታ ሲገልፁ የሚሰማ የንዝረት ስሜት አለ:: ለቁጥር የሚሰለቹትን ትተን ሀያ አመት የማይሞላው የአቢቹ ታሪክ ራሱ የሚገርም ነው:: በሀገራችን የሲኒማ ጥበብ ያደገ ቢሆን ኖሮ እንደ አቢቹ እና ደጃዝማች አበራ (የራስ ካሳ ልጂ) ያሉ ወጣቶች ከፈጸሙትም ጀብዱ ካሳዩት ወደር የሌለው መንፈሰ ጠንካራነት በተጨማሪ በማህበራዊ ግንኙነት አንፃር የነበራቸው ግንዛቤ አስተዋይነት እና የሀላፊነት ስሜት --- የጦር አውድማውን እና እንደ ወጣት ያሳዮትን ያመራር ብቃት የሚያንጸባርቅ ደህና ፊልም ተሰርቶበት ለትውልድ ጥሩ አስተማሪ ሊሆን ይችል ነበር::
በነዛ ጀግኖች ትውልድ እና በእኛ በእንዝህላሉ ትውልድ መካከል ያለውን ልዮነት ለመተንተን ሞከርኩ:: ባያረካኝም:: የድሮው ወጣት ወኔ አለው:: የሀገር ፍቅር አለው:: ፈሪሀ እግዚያብሄር አለው:: ምናልባት የባህል ወረራ ሰለባ ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ ነገር ይሆናል:: አሁን በግልጽ እንደሚታየው ወይ ወኔ የለም:: ወይ የሀገር ፍቅር የለም:: ወይ እምነት የለም:: ወይ ሁሉም የለም:: እነዚህን ሁሉንም አንድ ሰው ላይ ማግኘት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው:: የማህበረሰባዊ አስተሳሰብ እና ትኩረት ልዮነትም ይመስለኛል:: ከስነ-ጥበብ አቅም ከእኛ ቀደም ያሉት የሚያንጸባርቁት ፍጹም ሀገራዊ ስሜት እና ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸውን ነገሮች ነው:: ይሄን ለማስተዋል ቀደም ያሉትን የሙዚቃ እና የድርሰት ስራዎች ብቻ ማገላበጡ ይበቃል:: ስለ አርበኝነት ስለ ሀገር ፍቅር ኢትዮጵያውያን ስላደረጉት ደጋድሎ ይዘመር ነበር:: "እንኳንስ በህይወት እያለሁ በቁሜ ለሀገሬ ነጻነት ይዋደቃል አጽሜ"" የተቀነቀነው በ70ዎቹ አጋማሽ ወይ መጨረሻ ነበር:: የተደረገውን ተጋድሎ እየሰሙ ያደጉ ትውልዶች በመሆናቸው የሀገር ፍቅር ስሜት እና ለሀገር መጋደልን በባህሪ ስለወረሱ ይመስለኛል::

አሁን ዘመን ተቀይሯል::ገጣሚያን እና ጻሀፍት የሚያነሱት የሚጥሉት ነገር እንደምታዘበው የፍቅር አርበኝነት ነው":: የወጣቱ ተግባር "ማፍቀር ማፍቀር አሁንም ማፍቀር ነው"በሚል አይነት መንፈስ እንኳን አሁን እና ከአስራ አምስት አመት በፊት የነበሩ የልብ-ወለድ ድርሰቶች "የፍቅር አርበኝነትን" የሚያንጸባርቁ አይነት ነበሩ:: የ"ሀብታም ልጂ" የደሀን ልጂ ስታፈቅር ወይ ሲያፈቅር ወይ የሚወዳትን ልጂ ለማግኘት የተፈጠሩ መሰናክሎችን ሲያልፍ … "እምቡጥ ጽጌሬዳን ለምቅጠፍ እሾሁን ማለፍ ያስፈልጋል” አይነት ትረካ ያስነብቡናል ...." “ ውዴ አንቺኮ ማለት ለኔ ሁለ ነገሬ ነሽ”....”አንተ እኮ ማለት ማለት ‘ድቅ ድቅ ባለ ጨለማ ብርሀን ለመፈንጠቅ እንደምትወጣው ውብ ጨረቃ ነህ ...ህይወቴ ያላንተ ብርሀን አይኖረውም” ያስነብቡና እና መጨረሻ ላይ ገጸ-ባህሪ ጭምር ይገሉና የፍቅር አርበኝነቱም በሞት ተጠናቆ አሳዛኝ እንዲሆን ይደረጋል:: ጨለምተኝነት አና የአቸናፊነት ስነልቦና የማያውቀው ሆኖብኝ ቁጭ ይላል::የድሮዎቹ ወጣቶች የሚያነሱት የሚጥሉት (ሮማንቲሳይዝ የሚያደርጉት ሀገር እና ህዝብን ነው:: ) “አንቺ እኮ ማለት ለኔ” የሚሉት ኢትዮጵያን ነው:: አስተሳሰባቸው ርባና በሌለው ምክንያታዊነት የተበረዘ አልነበረም:: የህይወትን ትርጉም የሚያዮበት መነጸር ኢትዮጵያ ነበረች:: የፍቅር ህይወት የላቸውም ማለት አይደለም:: ለመለያየት ካለመፈለጋቸው የተነሳ ተያይዘው ጦር ግንባር የሚሄዱ ሁሉ ነበሩ:: የሚንቀለቀል የሀገር ፍቅር ስሜት በዛን ዘመን ከእድሜ ጋር እንኳን አብሮ የሚያረጂ አልነበረም:: የጦር ምክር ተደርጎ ለመዝመት ከተወሰነ በኍላ የኢትዮጵያ ገበሬ ወታደሮች በራስ ካሳ ፊት የገቡት ቃል ሁኔታውን የሚያመላክት ይመስላል:: በገጽ 50 ላይ እንዲህ ጽፎታል :-
"አንድ ቆፍጣና በራስ ካሳ የሜዳ ላይ ተንቀሳቃሽ ዙፋን ፊት ቀርቦ ጎራዴውን እያወናጨፈ 'በዚህ ጎራዴ አስራ አምስት አንበሶች ገድየበታልሁ: ሁለት እጥፍ ጣሊያንም እገላለሁ' እያለ ፎከረ:: ከማልረሳው ለመጥቀስ ያህል አንድ አዛውንት ጎራዴያቸውን እያወናጨፉ 'በዚህ ጎራዴ ከእምየ ምኒሊክ ጋር አስር ጣሊያን ገድያለሁ:: አሁንም መቶ እጥፍ ጣሊያን እገላለሁ" የሚለው ፉከራ አንዱ ነው:: ሌላው አንድ በግምት ሀያ አመት የማይሞላው ጎረምሳ ሲናገር "እኔ ወጣት ነኝ: ከዚህ በፊት ጀግንነቴንና ታማኝነቴን ለማሳየት እድል አልነበረኝም:: አሁን ግን ሀገሬን ሊወር የመጣን ጣሊያን እንደ ቆሎ አቆላዋለሁ:: አንዱንም አልምርም ሲል በስሜት ተናገር"" ገጽ 50- 51 [ የሀገር ፍቅር እና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ከትንሽ እስከ ትልቅ ተመሳሳይ እንደነበረ የሚጠቁም ይመስለኛል]

ሴት ወንድ ሳይል የሚያጠቡ ጭምር እንደዘመቱ የሚያመላክትም መረጃ አለ:-
...በዚህ እንደሞላ ወንዝ እያጓራ በሚጓዝ ጦር ውስጥም እንደነገሩ ሸማ የተከናነቡና በጀርባቸው በቅርጫት ሙሉ የማብሰያ ቁሳቁሶች ያዘሉ ሴቶችም ነበሩ:: የሚጠባ ልጂም የተቸከሙ ታይተዋል..."ገጽ 72

በዘመናችን ያለውን ወኔ ቢስነት ከመመዘን በፊት በዚያን ዘመን የታየውን ከልክ ያለፈ ጀግንነት ምክንያት መጠየቅ ያስፈልጋል:: የዚህ የጀግንነት ሚስጥር ምን ነበር?? ምናልባት ብዙ ትንተና እና ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ሊሆን ይችላል:: ብዙ ምርምር የማይጠይቀው ነገር ግን የሀገር ፍቅር ለክብር እና ለነጻነት የሚሰጥ ዋጋ ከምንም በላይ ደሞ በፈጣሪ ላይ ያለ ጠንካራ እምነት ይመስለኛል:: ክርስቲያኑ ከልቡ ክርስቲያን ነው:: እስላሙም እንዲሁ ከልቡ እስላም ነው:: ስለ ነበረው የእምነት ጥንካሬ ያንጸባርቃሉ ያልኳቸውን ልጥቀስ:-

...በጦር ሜዳም ሳይቀር መጸለይይቻላቸው ዘንድ እያንዳንዱ ከፍ ከፍ ያለ ሹም ሳይቀር የራሱን ቄስ የራሱን ነብስ አባት ይዞ ነው ወደ ጦር ሜዳ የመጣው:: ቄሶችም ሆኑ ሼኮች የራሳቸውን የሆኑ ወታደሮች ያላቸው ከመሆኑም በላይ በጦር ግንባር ሜዳም ጠመንጃ ይዘው ይሳተፋሉ …
….በጸሎታቸውም ያገራቸውን ድንበር በማን አለብኝነት ደፍሮ የመጣን የጠላት ሰራዊት ከሀገራቸው ጠራርገው ያወጡ ዘንድ እግዚያብሄር ብርታቱን ሰጥቶ ይረዳቸው ዘንድ ሳይታክቱ በየምሽቷ ይለምናሉ: ይማጸናሉ:: ... ' ጦራችንን ሰብቀን ጎራዴያችንን መዝዘን ጠመንጃችንን አንስተን እናባርራቸዋለን::ገጽ 166-167 [በእግዚያብሄር/በአላህ ርዳታ መሆኑ ነው::]

እንዲህ ያለ የሀገር ፍቅር እምነት እና ጀግንነት በበቀለበት ምድር ላይ ልብ የሚያደማም ከሀዲነት ይስተዋላል:: የሀይማኖት እና የቋንቋ ልዮነት ሳይኖር በህብረት የጣሊያንን ወራሪ ጦር ለመመከት ለኢትዮጵያ የነበረውን ታማኝት( ከኤርትራውያኖች ጭምር -ገጽ 138 ላይ እንደተመለከተዉ) እና ቁርጠኝነት ያህል ክህደትን መርጠው ኢትዮጵያን የወጉም ነበሩ:: ክህደት የአማኝ ህዝብ መገለጫ አይደለም:: ከጣሊያን ጋር የሞተ የትግል ሽረት ትግራይ ላይ ሲደረግ ራሳቸውን እንደሺፍታ አደራጂተው በእምየ ኢትዮጵያ ልጆች ላይ አደጋ የጣሉትን የጣሊያን ቅጥረኞች እና ባንዶች እንርሳቸው እንኳን ቢባል አሁን ያሉት ህወሀቶች እና ደጋፊዎቻቸው የሚሄዱትን አኳሄድ እና ባህሪ ከገንዘብ ጋር ያላቸው ትስስር እና አሁንም ድረስ ያለው ዘረፋ እንዳንረሳ ያደርገናል::

የኢትዮጵያ ጦር በጣሊያን ሰራዊት ለመፈታቱ የሀበሻ ጀብዱ ጸሀፊን ጨምሮ ሌሎች በቦታው ያልነበሩ ሰዎችም የሰጡት አስተያየት አለ:: ጣሊያን የትጥቅ እና ሎጂስቲክ የበላይነት ነበረው:: የጣልያን አየር ሀይል የተጫወተው ሚና አለ:: የመገናኛ እና የመረጃ ችግርም እንደነበረ በዚሁ በሀበሻ ጀብዱ ንባቤ ተረድቻለሁ:: ንጉሰ ነገስቱ ለሰላም በነበራቸው ተስፋ ምክንያት በመከላከል ላይ የተመሰረተ ውጊያ እንዲካሄድ ከማዘዛቸው ጋር ተያይዞ የንጉሰ ነገስቱን ትዕዛዙን ለመቀበል ብቻ ሲባል (ጠንካራ የዕዝ ማዕከላዊነት) ጣሊያኖችን ላይ በከበባ አደጋ መጣል እና ማሸነፍ እየተቻለ ጣሊያን ጊዜ እንዲገዛ እና ራሱን እንዲያደራጂ የሆነበት ሁኔታም እንደነበረ ተረድቻለሁ:: እንደዛም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ሰራዊት በተንቤን የመጀመሪያውን ጦርነት ካሸነፈ በኍላ በሁለተኛው የተንቤን ጦርነት ተሸንፎ እንደገና ሀይሉን አስተባብሮ ማይጨው ላይ ጣሊያንን ሲገጥም ለማሸነፍ ተቃርቦ እንደነበር ጸሀፊው ይናገራሉ:: የትግራይ ሽፍቶች ናቸው የተባሉት ግን ተመሳስለው ገብተው ከኍላ የምየ ኢትዮጵያን ጦር በማጥቃት የኢትዮጵያ ጦር እንዲሸነፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በዛ ላይ ተመሳስለው ገብተው ወሬ እየሰለሉ ለጣሊያን ሲያቀብሉ የነበሩትም እነሱው ናቸው:: ይሔ ደሞ ለጣሊያን ድል ጠቃሚ ሚና አልተጫወተም ማለት አይቻልም::

አሁንም የሀባሻ ጀብዱ ጸሀፊ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደሚነግሩን( በቦታው የነበረ እንደመሆኑ የበለጠ የሱ ሊያሳምን ይችላል) ራስ ሙሊጌታ ልጃቸውን (ከፈረንሳይ ሀገር ትምህርቱን አቋርጦ ሊዋጋ የመጣ ልጃቸው ነው) አስከትለው በፈረስ ወደ አሸንጌ እየተሻገሩ እያሉ ተደብቀው ተኩሰው የገደሏቸው ራሳቸውን የትግራይ ሽፍቶች ነን የሚሉ ነበሩ:: የወደቁትን አባቱን ሊያነሳ ከፈረስ የወረደው ልጃቸውም እንዲሁ በነዚሁ “ሽፍታ ነን” በሚሉ ከሀዲዎች እና ከይሲ አልሞ ተኳሾች ነው የተገደለው:: እንደሚገባኝ እንደዚህ አይነቱ ነገር ያለመረጃ ልውውጥ እና ስለላ የተሰራ ላይሆን ይችላል:: አንድ የኢትዮጵያን የጦር መሪ ---ራስን ያህል ነገር ሲገደል ከጣሊያኖቹ የሚኖረውን ሽልማት ልብ ይሏል::

በዚህ ክህደት እና ዘረኝነት ግራ የተጋባው ጸሀፊው የጠየቀው ጥያቄ እና ያገኘው መልስ እንዲህ ይነበባል:-
ከመሀል ሀገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው የነዚህን ሚስኪኖች [ዘራፊ ነን የሚሉትን እና የትግራይን ህዝብ] ህይወትና ንብረት ከጠላት (ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ: ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል? ስል በድጋሚ አቶ ኪሩቤልን ጠየኩት …
‘አብዛኛዎቹ የትግራይ ሰዎች ይሄንን የተቀደሰ ሀሳብ ይቃወሙታል’ አለኝና ቀጥሎ ‘አንዳንዶቹ ይሄ ከመሀል ሀገር የመጣው የአማራና የኦሮሞ ሰራዊት በትግራይ ከከረመ ያለውን አዝመራ ከብትና ፍየል ይፈጀዋል በለው ይፈራሉ:: ሌሎች ደሞ ጣሊያኖች እስካሁን የወረሩት የትግራይን ግዛት ብቻ ነው እናም ትግራይን ከጠላት ለመከላከል ብቸኛ መብት ያለው የትግራይ ሰው ብቻ ነው ብለው ያምናሉ:: …
...ቀጥሎም ጣሊያኖች ይኼንን ችግር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በአማራው እና በኦሮሞው ጦር ላይ ትግሬዎች መሳሪያ እንዲያነሱ በሰላዮቻቸው አማካይነት ሲሰብኩና እና የነገር እሳት ስቆሰቁሱ እንደከረሙ ጨምሮ ነገረኝ:: ገጽ 121- 122

ሌላ ቦታ ላይ ደሞ እሱ (አዶልፍ ፓርለሳክ) በነበረበት ቦታ ያጋጠመውን እንዲህ ጽፏል :-
...እኛ [እሱ እና ሌላ አውሮጳዊ] እንዲህ በትዝታ ርቀን ከጦር ሰፈራችን ራቅ ብሎ አልፎ አልፎ ድው! ድው!ደው! የሚሉ የተኩስ ድምጾች እንሰማለን:: እዚህም የትግራይ ሽፍቶች ለዘረፋ ይመጣሉ:: ምን ያድርጉ! ጣሊያኖች በመሳሪያና በገንዘብ ይረዱአቸዋል:: ለዚህም ይመስለኛል በደጃዝማች አበራ ዋሻ ደጃፍ ሁለት አነስ አነስ ያሉ መትረየሶች የተጠመዱት::
የትግራይ ሺፍቶች ብዙ ጊዜ በድፍረት እስከ ጦር ሰፈራችን እምብርት ድረስ ዘልቀው ለመዝረፍ ሞክረዋል:: ሽፍቶችን ከሌላው የባላገር ወታደር መለየት አስቸጋሪ ነው:: ሽፍቶቹም ልክ እንደባላገሮቹ ወታደሮች ሁሉ የሚለብሱት ያደፈ ሸማ ነው:: እና በመጀመሪያ እይታ ማንም ሰው ሽፍቶች መሆናቸውን መገመትም መለየትም አይቻለውም:: ገጽ 149

እንዲህ ያለው ክህደት እና ዝርፊያ ነጻነት ሲመለስ ያስከተለው ነገር እንደሚኖር መገመት አይከብድም:: የአጼ ኃይለስላሴ መንግስት “ሆደ ሰፊነት” በሚል ፈሊጥ በባንዳዎቹ ላይ ሀጢያታቸው እንዲበዛ ባያደርጉም በባዶ እግሩ ትግራይ ድረስ በመከራ ሊዋጋ ሄዶ ክህደት የጠበቀው እና በከሀዲወች በመንፈስም በስጋም የደማው የባንዳ ወገን የነበረባቸውን ቢጎስም እና ብድር ቢመልስ በኍላ መልኩን ቀይሮ የብሄር ጭቆና ታርጋ ተለጥፎለት መጡ:: “የብሄር ጭቆናም” ተብሎ ከቀዳማዊ ወያኔ እንቅስቃሴ ወጣ የሚባለው የባንዳዎች የመንፈስ ልጂ ህወሀት ሊታገል ሲነሳ አሁንም “ትግራይን ነጻ በማውጣት” በሚል ፈሊጥ ነበር:: በትግራይ የነበሩ የአርበኛ ልጆችም የፕሮፓጋንዳውን ምንጭ እና ዘዴ ሳይገባቸው ከህወሀት ጋር አብረው እንዘጭ እንዘጭ ብለው አንዳንዶቹ በስተመጨረሻ ህይወታቸውን አጡ:: አንዳንዶቹ ተባረሩ::


አነሳሴ በመጻሀፉ ላይ ያስደመሙኝን አንዳንድ ነገሮች ማካፈል ቢሆንም እያነበብኩ እያለሁ በማገናዘብ ብቅ የሚል ስዕል የነበረኝን ጥርጣሬ እንድገፋበት አደረገኝ:: ህወሀቶች ከየት እንዴት እና ለምን እንደመጡ የሚጠቁም (እንደጠቆምኩትእንደዛ ተብሎ የተጻፈ የለም ---ስንተነትን ግን የምናገኘው ይሄንኑ ነው::) ሳልጠቅስ ማለፍ እንደሌለብኝ አመንኩ:: ከደርግ በኍላ የአርበኛ ልጆች በነበሩ ጭምር ተከልለው ወደ ስልጣን የመጡት የባንዳዎቹ ልጆች የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከነደፉት ጎሳን ያማከለ የፖለቲካ አደረጃጀት ሌላ በ 'ህገ-መንግስት" እና በአዋጂም ጭምር ሊያጠፉት ሞከሩ:: እጂግ በጣም የሚገርመው ነገር በባዶ እግራቸው ለረሀብ እና ለሌሎች ችግሮች ሳይበገሩ ከዘመናዊ ጦር ጋር የተጋደሉትን እና ከሀገር በላይ የማይወዱትን ነብሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን በመጥፎ ሁኔታ ስሎ የጀግንነት መጀመሪያ እና መጨረሻ ተምሳሌት የህወህት ታጋይ ይመስል ጧትና ማታ ስለ ህወሀት ጀግንነት በትግሪኛ እና በአማርኛ ተለፈፈ በቴሌዝዥን እና በራዲዮ እንድንሰማ ተደረገ:: በዚህ ሂደት ውስጥ እውነተኛዎቹን ለኢትዮጵያ የደሙትን የሞቱትን ጀግኖች በትግራይ መሬት ከጥሊያን ጋር ሲዋደቁ እዚያው በዱር በገደል የወደቁትን ጀግኖች እንዳይነሱ ተደረገ:: ተርጓሚው በእውነት ይሄንን ስራ ለዚህ ትውልድ በማበርከቱ ትልቅ ስራ ሰርቷል:: በህወህት ዘመን ተወልደው ህወሀት ""ጀግና ነኝ:: ጀግና ተፈጥሮ አያውቅም እያለ"" ሲለፋደድ እየሰሙ ያደጉት እና ዛሬ በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለውን ስራ እንዲያነቡ መምከር ያስፈልጋል ባይ ነኝ:: አምላክ ብርታትን ሀይልን ይስጠን::


2 comments:

  1. "አንድ ቆፍጣና በራስ ካሳ የሜዳ ላይ ተንቀሳቃሽ ዙፋን ፊት ቀርቦ ጎራዴውን እያወናጨፈ 'በዚህ ጎራዴ አስራ አምስት አንበሶች ገድየበታልሁ: ሁለት እጥፍ ጣሊያንም እገላለሁ' እያለ ፎከረ:: ከማልረሳው ለመጥቀስ ያህል አንድ አዛውንት ጎራዴያቸውን እያወናጨፉ 'በዚህ ጎራዴ ከእምየ ምኒሊክ ጋር አስር ጣሊያን ገድያለሁ:: አሁንም መቶ እጥፍ ጣሊያን እገላለሁ" የሚለው ፉከራ አንዱ ነው:: ሌላው አንድ በግምት ሀያ አመት የማይሞላው ጎረምሳ ሲናገር "እኔ ወጣት ነኝ: ከዚህ በፊት ጀግንነቴንና ታማኝነቴን ለማሳየት እድል አልነበረኝም:: አሁን ግን ሀገሬን ሊወር የመጣን ጣሊያን እንደ ቆሎ አቆላዋለሁ:: አንዱንም አልምርም ሲል በስሜት ተናገር"" ገጽ 50- 51 [ የሀገር ፍቅር እና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ከትንሽ እስከ ትልቅ ተመሳሳይ እንደነበረ የሚጠቁም ይመስለኛል]

    ReplyDelete
  2. "አንድ ቆፍጣና በራስ ካሳ የሜዳ ላይ ተንቀሳቃሽ ዙፋን ፊት ቀርቦ ጎራዴውን እያወናጨፈ 'በዚህ ጎራዴ አስራ አምስት አንበሶች ገድየበታልሁ: ሁለት እጥፍ ጣሊያንም እገላለሁ' እያለ ፎከረ:: ከማልረሳው ለመጥቀስ ያህል አንድ አዛውንት ጎራዴያቸውን እያወናጨፉ 'በዚህ ጎራዴ ከእምየ ምኒሊክ ጋር አስር ጣሊያን ገድያለሁ:: አሁንም መቶ እጥፍ ጣሊያን እገላለሁ" የሚለው ፉከራ አንዱ ነው:: ሌላው አንድ በግምት ሀያ አመት የማይሞላው ጎረምሳ ሲናገር "እኔ ወጣት ነኝ: ከዚህ በፊት ጀግንነቴንና ታማኝነቴን ለማሳየት እድል አልነበረኝም:: አሁን ግን ሀገሬን ሊወር የመጣን ጣሊያን እንደ ቆሎ አቆላዋለሁ:: አንዱንም አልምርም ሲል በስሜት ተናገር"" ገጽ 50- 51 [ የሀገር ፍቅር እና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ከትንሽ እስከ ትልቅ ተመሳሳይ እንደነበረ የሚጠቁም ይመስለኛል]

    ReplyDelete

Blog Archive