Monday, March 1, 2010

አደዋ !

ነገረ አድዋ ...ጥልቅ ; ምጥቅ
ጸአዳ ዝንት -ዓለም የሚያንጸባርቅ

የወራሪ የታሪክ ለምጥ
የአበሽ የታሪክ ጌጥ
የአበሽ ተድላ ሀሴት
የወራሪ የመንፈስ ; የአካል ስብራት

አድዋ የቀን አውራ
የድል አባወራ
እንዳውዳመት ይዘከራ !

የድል ብስራት
የድል ጥሪት
የመንፈስ ስንቅ ያበሻ አንጡራ ሀብት

አድዋ !
የወንድነት ድካ ያበሽነት ልክ ስፍር
የአበሽ የድል ገድል ! የድል ስንክሳር
የድል ችቦ ክምር
የማይበገር ጀግና ትውልድ
የደም ; ያጥንት ውልድ
ሲያስቡት መንፈስ እንደ ችቦ የሚያቀጣጥል የሚያነድ
የኛነታችን ማህተም የኛነታችን አሻራ
የመንፈስ መጽናኛ በሌሎች ጥቁር ሕዝቦችም ጎራ

አድዋ !

የአበሻነት እና ""የነጻነት "' የቃል ኪዳን ውል
የእምቢ ለሀገሬ እምቢ ለነጻነቴ ብሂል
የሚንበለበል ያገር ፍቅር ምስል
"ዋ ኢትዮጵያ ! እኔ ላንቺ ልሙት እረ ልከንበል "
ይሄ ነው ያድዋ ትርጉሙ
ሃበሻ የጻፈው የሳለው በደሙ

ሰው ሲደመም ጡብ ;ሲሚንቶ ;ፌሮ ተስማምቶ ሰማይ ሊነካ ሲንጠራራ
አበሽ በዛቱ ; በልቡ የማይፈርስ ሰማይ ጠቀስ የድል ክምር ሲሰራ
የሚታይ ከየትኛውም ስፍራ ...
እኛማ ለምን አንኮራ !!

አድዋ ትዕይንትም ነው
በአንድ በኩል ቀልበ ጡሊ የሰው አገር ሊወር የወበራ
በሌላ በኩል ገራገር አበሽ ግን ለነጻነቱ የማይመለስ ሞት የማይፈራ
ስንት የሴት ወንድ ; ስንት የወንድ አውራ
ጎራዴ የያዙ እጆች የተፋለሙበት ከባለመትረየስ ጋራ
የስጋና የመንፈስ ስምምነት የ "ልሙት ለሀገሬ ፍካሬ '
የጽኑ ነብስ ; ጽኑ ስጋ የመንፈስ ዝማሬ ; የተጋድሎ ፍሬ
ያገር ፍቅር እና አልሸነፍ ባይነት
ወራሪን እንደ ሰንጋ የመተሩበት
ያበሻ ማንነት የታየበት
ዝንታለም የሚታወስ ትዕይንት

አደዋ !

የአድዋስ ቅዱስነት !!!
እንደ ክርስቶስ ስቅለት
ለሰው ልጂ ፍቅሩን እንደገለጠበት
አበሻ "ለነጻነት ' ያለውን ቀናዒነት ያሳየበት
የደም ; ያጥንት አስራት በኩራት ያስገባበት
የነጻነት የመጨረሻ ዋጋ -ህቅታውን ከነዛቱ የሰጠበት
የድል ጥሪት ;
የአበሽ መንፈሳዊ ሀብት !!
የሀበሻ ኩራት !!

አድዋ የድል አውራ
እንደ አውደ ዐመት ይከበራ !!

Blog Archive