Monday, February 28, 2011

የዳቦ ወይስ የፖለቲካ ጥያቄ?

ድሮ ኮተቤ ኮሌጅ ስማር የረሀብ አድማ ተደርጎ ነበር:: በጊዜው የነበሩት የተማሪዎች መማክርት አባላት የህዋሀት አባልና አንዳንዶቹም ታጋይ የነበሩ ናቸው:: በደንብ አስታውሳለሁ እነዚህ አመራሮች የተሰበሰበውን ተማሪ የተጀመረው አድማ መቶ በመቶ ከምግብ አቅርቦት ጥራት ጋር የተያያዘ እንደሆነ እና የፖለቲካ ጥያቄ እንዳልሆነ አጽኖት ሰጥተው ""ፖለቲካ ከተነሳ በየለሁበትም""አይነት መንፈስ ተማሪውን ያስጠነቅቁ ነበር:: ከዚያም መፈክር ይጻፍ ተብሎ በአራት ቋንቋ ተጻፈ:: የማስታውሳቸው ""ረሀብ ጊዜ አይህብን"" ""ጋፊን ኬኛ ጋፊ እኛታቲ"" ""ጥያቄያችን የዳቦ ነው"" እና ""we demand bread"" ነበሩበት:: እውነት ለመናገር የዳቦ ችግር አልነበረም:: በእኛ ሀገር ስታንዳርድም ይቀርብልን የነበረው ምግብ አድማ የሚያስመታ አልነበረም:: እርግጥ ነው የካምፓስ ምግብ የጣዕም ችግር አለበት:: እሱ ደሞ ሀገራችን ደሀ እንደመሆኗ አድማ የሚያስመታ ጉዳይ አልነበረም:: በኍላ ሲገባኝ የምግብ ጥራት እና ""ጥያቄያችን የዳቦ ነው"" ጩኽት ትክክለኛ ምክንያት አልነበረም:: ጥያቄያቺን ""የፖለቲካ አይደለም"" የሚለውም ሀሳብ እንደዚያው::
ለአድማ ያነሳሳው ትክክለኛ ጉዳይ የታፈነ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ችግር ነበር::

በ1992 ዓመተ ምህረትም አገሪቱን ሊያነቃንቅ የሞከረ የተማሪዎች አመጽ ተከስቶ ነበር:: የህዋሀት መንግስት ከ40 በላይ ንጹሀን ዜጎችን ገድሎበታል:: የዚህኛውም አመጽ ጥያቄ እንዲሁ ዙሪያ ጥምጥም ነበር:: ""የአካዳሚክ ነጻነት"" ጥያቄ ነበር በዋነኛነት የተስተጋባው:: ወያኔም እንደለመደው ያለ እፍረት ""ጥያቄው የአካዳሚክ ጥያቄ አይደለም:: የፖለቲካ ለውጥ ሊያመጡ የፈለጉ ኃይሎች ናቸው ያንቀሳቀሱት"" የሚል አስተሳሰብ ይዞ ተማሪውን የዘር ፖለቲካ በማራገብ ሊከፋፍለው ሞከረ:: ምናልባት ብዙዎቹ የፌስ ቡክ ጓደኞቼ የዚያ እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ በመሆናቸው ከላይ ያልኩትን ነገር እንደሚያስታውሱት እገምታለሁ::

ታዲያ ዛሬም ድረስ የማይገባኝ ነገር የአንድ ሀገር የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች ; በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ የሀገሪቱ የወደፊት ተስፋ እና ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን ቀጥተኛ የሆነ የፖለቲካ ጥያቄ መጠየቅ የማይፈቀድላቸው ለምንድን ነው?? እንደ ዜጋ የፖለቲካ መብት የላቸውም ወይ??

የኮተቤው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲደረግ ወያኔ በጎጃም ገበሬዎች ላይ ይሄ ነው የማይባል ከፍተኛ በደል አድርሶባቸው ስሞታ ለማሰማት አዲስባ ድረስ የመጡበት ሁኔታ ነበር:: ተማሪው በገበሬው ላይ በተደረገው ነገር ተቃውሞን እና ሀሳቡን እንኳን እንዲገልጽ አልተፈቀደለትም ነበር:: ለምን? "" የፖለቲካ ጥያቄ"" ስለሆነ::

በተመሳሳይ ሁኔታ የ1992ም የአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ተማሪዎች ""የአካዳሚክ ነጻነት"" እንቅስቃሴ ከመደረጉ ትንሽ ቀደም ብሎ ወያኔ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በተለይም በኦሮሚያም በዜጎች ላይ ሽብር ይነዛ ነበር:: ዜጎች የኦነግ አባል ናችሁ እየተባሉ ቁም ስቅል ያዮ የነበረበት ጊዜ ነበረ:: ከኦሮሚያ አካባቢ የመጡ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት እንዴ በዮኒቨርሲቲው ጊቢ እስቅስቃሴ ሲያደርጉ የአጋዚ ሰራዊት በጨለማ ገብቶ የህዋሀት አባል ተማሪዎች መሪ ሆነው የተማሪ ወታወቂያ እየታየ ተማሪዎች ወደ እስር ተግዘዋል:: እንዲህ እንዲህ አይነት ወያኔ የሚወስዳቸው የፖለቲካ አካሄዶች ያለጥርጥር በወያኔ ፖለቲካ ላይ ጥያቄ ያስነሳሉ:: በሌላ በኩል የዮኒቨርስቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ጥያቄ እንዲጠይቁ አይፈቀድላቸውም:: ""ጥያቄያችን የዳቦ ነው"" እየተባለ እስከመቼ ነው የሚኖረው?? የነገ ተስፋችን በማን እጂ ነው ያለው??


ሰሞኑን የግብጽ እና የቱኒዚያ ወጣቶች አብዮት አካሔዱ ብሎ የወያኔ መንግስት ሺብር ስለገባው ; ወላጆችን ሰብስቦ ልጆቻችሁን ያዙ እንዳለ ሰምተናል:: ሚገርመው ወላጆች ልጆቻቸውን የሚይዙት እኮ የፖለቲካ ጥያቄ እንዳያነሱ ነው:: በሌላ በኩል ይሄው መንግስት የኢትዮጵያ ወጣቶችን በተለያየ መልኩ እያደነዘዘ የፖለቲካ ድንፈፍ ሊያደርጋቸው እየሞከረ ነው::ቅጥ ያጣ ነቀት ማለት ይሄ ነው:: በወያኔ መንግስት ላይ ወጣቶች ሊያነሷቸው የሚገቡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ::

እኔ ግን በዋነኛነት የምጠይቀው የህወሀት መንግስት የኢትዮጵያን ወጣቶች በስራ እድል እና በጥቅማጥቅም በመያዝ ታማኝ የስርዓቱ ተገዢዎች እንዲሆኑ የወሰደው እርምጃ ነው:: ኢትዮጵያውያን ዜጎች የትምህርት ደረጃቸው በሚፈቅድላቸው መጠን የመንግስት የስራ ዕድል የማግኘት መብት አላቸው:: ይህንን ህጋዊ መብታቸውን ዘንግተው ለስራ እድል ተብሎ የፖለቲካ እምነታቸውን መቸርቸር እና የማያምኑበትን የፖለቲካ እሳቤ እንዲያራምዱ መደረግ የለባቸውም:: የህዋሀት መንግስት በጉልበት እያስተዳደረው ባለው የኢትዮጵያ ሀብት የፖለቲካ መነገጃ የስራ ዕድል መፍጠሩ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንደውለታ መታየት የለበትም :!: ህዋሀት ከኪሱ የከፈለበት ጉዳይ የለም:: እንደውም ባለፈው ከአቶ ስብሀት ነጋ በቪኦኤ እንደሰማነው ህዋሀት የትየለሌ የሆነ ሀብት እንዳጋበሰ ነው:: ያ ተረስቶ ጭራሽ ለኢትዮጵያውያን ውለታ እንዳደረገ ማሰብ ምን ያህል የፖለቲካ ድንዝዝነት እንደነገሰ ብቻ ነው የሚያሳየው::

እስከዛሬ ድረስ ቀጥተኛ የሆነ የፖለቲካ ጥያቄ ባለመጠየቅ ; የህዋሀት መንግስት የሀገሪቱን ሀብት እና ንብረት እንደፈለገው ሲያደርገው በመቆየቱ ህዋሀት የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ውለታ አለበት:: ከገባው:: ህዋሀት ከስልጣን ከወረደ የተገኘው የስራ ዕድል ይጠፋል ብሎ ማሰብ የፖለቲካ ሞኝነትም ነው:: የኢትዮጵያ ወጣት ተስፋ ነገውን በእጁ በማስገባት እና ባለማስገባት ላይ የተመሰረተ ነው:: በህዋህት የፖለቲካ ዳረጎት አይደለም!! ህዋሀት ከስልጣን ቢሽቀነጠር ቀን የሚጭልምበት ኢትዮጵያዊ አይኖርም:: ከጨለመ የሚጭልመው ለራሱ ለህዋህት ብቻ ነው:: የፖለቲካ ለውጥ ደሞ ያስፈልጋል::ሀያ አመት ሙሉ የዘር ነጋሪት እየመታ ""በብሄር ብሄረሰቦች"" የማደናገሪያ ስልት የፖለቲካ ስልጣን በማያፈናፍን ሁኔታ ይዞ ሲዘርፍ ከኖረ የፖለቲካ ቡድን ነጻ መውጣት በራሱ ትልቅ ስኬት ነው:: ነጻነት የሌለው ወጣት ተስፋ አለኝ ሊል አይችልም! የደስታ ሆነ የስኬት; የተስፋ መሰረቱ ነጻነት ነው:: ነጻነት የሌለው ሕብረተስብ የትም ሊደርስ አይችልም::

No comments:

Post a Comment

Blog Archive