Tuesday, February 15, 2011

ወይ ቫለንታይን?!

ሰው የመሆን ትርጉም የሚያጎላው ማሰብ እና ማገናዘብ መቻል ነው:: ከሌላው ፍጥረት የምንለይበትም ምክንያትም ይሄው ነው:: የሚያስብ እና የሚያገናዝብ ሰው ደሞ እንዳረጉት አይሆነም:: ይጠይቃል:: ""ለምን?"" ይላል:: ባለፈው በዚሁ በፌስ ብክ ፔጄ ላይ "" ዘመን የሰጠን እና የወሰደብን ነገር ምንድን ነው?"" የሚል የመወያያ ርዕስ አንስቼ የፌስ ቡክ ጓደኞች የጠበኩትን ያህል መልስ አልሰጡበትም:: እንደውም ምንም አልመለሱም:: የግብጽ ወጣቶች ሰሞኑን ትንግርት አሳይተውናል:: ዘመናዊነት የሰጣቸውን የቴክኖሎጂ ጥበብ -ኢንተርኔትን ተጠቅመው - አገሬን እወዳለሁ ይል የነበረ መሪያቸው ( ሙባረክ) የወሰደባቸውን ነጻነት በጽናት ታግለው አስመልሰውታል:: ሙባረክ የወሰደባቸውንም የትየለሌ ገንዝብ ለማስመለስ በዝግጂት ላይ ናቸው:: የተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎች የሚገባቸውን መብት እንዲያገኙም ትግላቸውን ቀጥለዋል:: የግብጽ የለውጥ አብዮት አልቆአል ማለት አይደለም:: ከሁኔታቸው እንደተረዳሁት ትግሉን እዚህ ቦታ ላይ በቁሙ የሚጥሉትም አይመስለኝም:: እንዳልሆነ ሆኖ ሊሰበር ስለሚችል:: የግብጽ ወጣቶች የነጻነት ትግል መንፈስ ግን መንፈሳዊ ቅናት ያሳድራል:: የግብጽ ወጣቶች በዘመናቸው ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሞክረዋል:: ዘመን እስከመጨረሻው ባሪያ እንዲያደርጋቸው አልፈቀዱለትም:: የግብጽ ወጣቶች ይሄንን ሁሉ ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ውስጥ የቫለንታይንን ቀን ለማክበር በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ነጋሪት ይጎሰም ነበር አሉ:: አዲስ ነገር ኦንላይን ላይ ስለ ቫለንታይን ቀን የተጻፈውን አንብቤ በጣም ተገርሜአለሁ::
ወጣቱ እንደዚህ እንደዚህ አይነት -ከልብ ሆነው ሲያስቡአቸው ትርጉም የማይሰጡን አውሮፖዊ አስተሳሰቦች እና ባህሎች የሙጥኝ እያለ በያዘ ቁጥር; ትርጉም ያላቸውን እንደ ነጻነት ያሉ እና የሀገር ጉዳዮችን ቸል እያለ እና ከናካቴውም እየረሳ ይመጣል:: በመርህ ደረጃ ስናየው ፍቅር የበለጸጉ ሀገሮች ያወጡት ኮንቬንሺናል ቀን ያስፈልገዋል ወይ የሚለው ራሱ አንድ ጥያቄ ነው:: በባህልም በእምነትም እንደማውቀው ፍቅር የዕለት ተዕለት ጉዳይ ነው:: ያለፍቅር አይዋልም አይታደርም:: በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ:: እርግጥ ነው ስጦታ ፍቅርን ይገልጽ ይሆናል:: ሀዲስ አለማየሁም ""ለሚወዱት ሰው የሚደረግ ስጦታ ከሚቀበለው ሰው ይልቅ የሚሰጠውን ሰው ልብ የበለጠ ያስደስታል"" ብለው ጽፈዋል:: ያስማማል:: ጥያቄው ግን የፍቅር መግለጫ ስጦታ ለመለዋለጥ እና ፍቅርን ለመግለጽ February 14 አይዲያል ነው ያለው ማን ነው? የቫለንታይንን ቀን myth የፈጠረው ማን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: ስፔሻል የሆነ ቀን ከሆነ የሚፈለገው ""በኮንቬንሽን ደረጃ የሚከበርን ቀን የወል ይሆን እንደሁ እንጂ የግል ሊሆን አይችልም::
ከተጨባጭነት ስናየው ደሞ አውሮፖዎቹ እና አሜሪካዎቹ (ሌሎችም የበለጽጉ የእስያ ሀገሮች) የቫለንታይንን ቀን ቢያከብሩም የኢኮኖሚ ሁኔታቸው ይፈቅድላቸውል:: ጦሙን የሚያድር እና ስራ አጥ ማህበረሰብ በበዛበት ምድር ከአውሮፓዎቹ እና ከሌሎች ከሞላላቸው ሀገሮች እኩል የምናብ ቫለንታይንን የሚከበርበት ምክንያቱ ሊገባኝ አልቻለም:: ከላይ የጠቀስኳቸው ማህበረሰቦች ወጣቶች በተወሰነ መልኩ ምርታማ ናቸው:: ከዚያም ባለፈ የት ገባችሁ የት ወጣችሁ ምን አሰባችሁ የሚላቸው ጉልበተኛ መንግስት የለባቸውም:: የመንቃት እና ያለመንቃት ዕድሉ ያለው በእጃቸው ነው:: እኛ ጋር ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሌላ:: ባለፈው ሳምንት ሀገር ቤት ስልክ ደውየ የማልጠብቀው የቅርብ ሰው ""የወያኔነት"" ፎርም ሞላሁ አለኝ:: ለምን እንደዛ ሆነ ብየ ስጠይቅ በቃ እንደዛ ካልሆነ ተምሮ ስራ ማግኘት አልተቻለም የሚል መልስ ነው ያገኘሁት:: የአንድ ሀገር ወጣት በዜግነቱ እና በችሎታው የስራ ዕድል ለማግኘት የማይችልበት ዘመን ላይ ተደርሷል ማለት ነው:: ግፈኛ የሚባለውን የደርግ አገዛዝ በደንብ አድርጌ አስታውሰዋለሁ ስዎች ስራ ለመያዝ የደርግ ፓለቲካ ደጋፊ መሆን እንዳለባቸው አላስታውስም:: አሁን ያለው መንግስት ግን በግልጽ ስራ አጥነትን ራሱ አስፋፍቶ ; የስራ ዐድልን ደሞ የፓለቲካ መነገጃ አደረገው:: የደርግ መንግስት ደሀ ነበረ:: የመንግስት ድርጂቶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ:: ንብረትነቱ የደርግ ፖርቲ የሆነ የንግድ ተቋም እንደነበረ ግን አላስታውስም:: አንድ ጊዜ አቶ ስብሀት ነጋ የሚባሉት የህዋሀት ሰው በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ አገልግሎት ላይ እንደተናገሩት የህዋህት ፓርቲ እጂግ በጣም ሀብታም ነው ; መገመትም ያስቸግራል ነው ያሉት:: ይሄ ሁሉ ሀብት የተገኘው ደሞ በዛች በደሀ ሀገር ስም እና ከዛች ከደሀ ሀገርም ነው:: ስራ አጥነት ግን ተንሰራፍቷል:: ኢትዮጵያን የሚመራው የወያኔ/ህዋሀት መንግስት ደሞ ዜጎች ስራ ለማግኘት እንደ ዜጋ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ; የህዋሀት እና እህት ድርጂቶች ፓርቲ አባል መሆን እንደሚጠበቅባቸው እየነገረ ስራ ሲሰጥ ; ወጣቱ ህዋሀት/ኢሀዴግን እንደባለውለታ ሁሉ ያይ ጀመር አሉ:: ሚያሳዝነው ረሀቡንም ስራ አጥነቱንም የፈጠረው ( ቢያንስ ያስፋፋው) ሀዋሀት/ኢሀዴግ ሆኖ ሳለ; ይሔው ፖርቲ በፖለቲካ ወገንተኝነት መመዘኛ የስራ ሰጪ ሲሆን በጎ አድራጊ መንግስት ሁሉ ሆኖ ቁጭ አለ:: እንዳረጉት መሆን ማለት ይሄ ነው:: ይሄንን ለማሰብ ያልቻን ወይ ያልፈለግን ደርሰን ከሞላላቸው እኩል ""ቫለንታይን" ላይ ስንጠላጠል የሚገም ነገር ነው::

ዛሬ የቫለንታይንን ቀን ምክንያት አድርጌ አነሳሁት እንጂ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ሲከበር አዲስ አበባ ሻራተን ጠጠር መጣያ እስከሚጠፋ ሰው ሞልቶ አበሻው የፈረንጆችን በዓል ቁጥር እይቆጠረ አክብሯል:: ""የኢትዮጵያ ቴሌቭዢንም"" ስርጭቱን በቀጥታ አስተላልፏል:: የምናስብ ትውልዶች ነን ለማለት ማስረጃ ማግኘት ሁሉ እየከበደኝ ነው:: ያ ሁሉ ነገር ሻራተን አዲስ ቢቀርም ኖሮ እኮ አንድ ነገር ነበር:: ሌላኛው ያልገባው ወጣት እንዲጓጓለት ተደርጎ በቀጥታ በቴሌቭዥን መተላለፉ ነው የሚያስቆጨው:: በየገጠሩ እና በክፍለ ሀገር ከተሞች ያለው ወጣት ያንን እያየ ኢትዮጵያ "አድጋለች"" እያለ እንዲሳሳት እና ማንነቱ እንዲወናበድበት እየተደረገ ነው ያለው:: ከታች ያለውን ክሊፕ ተመልከቱ::

http://www.youtube.com/watch?v=VceDMjlfLdQ

የኢትዮጵያውይንም ገና እየተረሳ "' x-mass'" ላይ ትኩረት እየተሰጠ እንደመጣ ነው የሚሰማው:: ትውልዳችንን እንዳረጉት እየሆነ ነው:: የሚያደርጉት ደሞ ራሱን ሳይሆን ሌላ አይነት::እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ ዝም ብለን በዘመን ተጽዕኖ ሂሳብ መያዝ አለብን? ነው ጠንከር ያለ ነገር አለ?? ማነው እየመራን ያለው? ወዴት ነው እየተመራን ያለነው? አሁን የተያዘው አካሄድስ ያስፈልገናል ወይ? የኢትዮጵያ ባህል አደንዛዥ ነው ጎታች ነው ...ምናምን ምናምን እየተባለ ሌላ አንደንዛዥ የሰው ሀገር ባህል እና አስተሳሰብ ያስፈልገናል ወይ? በእርግጥ የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው? ማንስ ነው የሚተረጉምልን? የደስታ ምንጩ ምንድን ነው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ብንለዋወጥ በጣም ደስ ይለኛል ::

No comments:

Post a Comment

Blog Archive