Sunday, March 17, 2013

ህወሓት ስለምን ሰልፉን ለመከልከል ፈለገ?

ለግራዚያኒ የሚቆመውን መታሰቢያ ሃውልት በመቃወም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ህውሓት ያደርጋል ብየ የወሰድኳቸውን ግምቶችን ውጨ በ"ምን ያደርግ ይሆን?" ስሜት ስጠባበቅ ነበር። ዛሬ ጊዜው ደርሶ የሆነውን ሰማን። ስለ እውነት ለመናገር የህወሃት መራሹ መንግስት ሰልፉን ሳያስተጓጉል ቢፈቅድ ኖሮ ብዙ ጊዜ ህወሓት ተለክፎበታል የምለውን የበታችነት ስነ-ልቦና ልክፍት ትክክለኛነት ራሴን ለመጠየቅ እጀምር ነበር። ሰማያዊፓርቲ ከሌሎች ከባለራዕይ ወጣቶች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር የጠራውን ሰልፍ የህወሃትን ስነ-ልቦና በእጂጉ የሚያደማ እንደሆነ ግልጽ ነበር ለኔ። የተቃውሞ ሰልፉ ከፖለቲካዊ ፋይዳው ይልቅ ስነ-ልቦናዊ ፋይዳው የህወሃትን ሂሊና እንደሚበጫቀጭው ግልጽ ነበር ለኔ። ይሄ ጉዳይ በ"ባለራዕዮ" መሪ "ራዕይ" ላይ የተቃጣ ጥቃትም ሊሆን ይችላል- ለሕወሓት (በትክክል ወይንም በስህትተ)። ሰልፉ እንድምታው በደንብ ከተጤነ ህወሓትን እንደፖለቲካ ቡድን የሚያሳንስ ስልፍ ነበር። እኛ (ከህወሓት ወገን ያልሆነው) በየካትቲ ወር በሶስት ቀን አዲስ አበባ ላይ ብቻ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሰውተውብናል- ዛሬ ለተቃውሞ በተወጣበት ግለሰብ ምክንያት-- በዋነኛነት ምክንያቱ የልግዛ አልገዛም ቢሆንም። ህወሓት ደሞ ጀግና ነኝ እያለ ወደ ላይ የሚዘልበት ጉዳይ በ17 ዓመት ከደርግ መንግስት ጋር ባደረኩት ትግል 60 000 የትግራይ ልጆች ሰውቻለሁ እያለ ነው።

የኢትዮጵያውያን ትግል በሆነ መልኩ በተዘከረ ቁጥር የህወህት የታላቅነት ቅዠት መሬት ይልሳል። በተጨማሪ የህወሓት ፖለቲካ ከወራሪው ጣሊያን ፓለቲካ ጋር የሚያገናኘው ቢያንስ ሁለት ያህል ታሪካዊ ትስስር አለ። አንደኛ ህወሓት ወደ ስልጣን ሲመጣ አክርሮ የያዘው የጎዛ ፓለቲካ ጀማሪዎቹ ጥሊያኖች ነበሩ። ኢትዮጵያ ታደርግ የነበረውን ጸረ-ጣሊያን ትግል ለማዳከም ጣሊያን ከወሰዳቸው የፖለቲካ ርምጃዎች ዋነኛው ኢትዮጵያን በዘር ላይ በተመሰረተ ክልላዊ አስተዳደር መከፋፈል ነበር- ልክ ህወሓት በስራ ላይ ያዋለው ዓይነት። ሁለተኛ - በህወሓት የትጥቅ ትግል ( እነሱ እንደሚሉት"ሁለተኛው ወያኔ እንቅስቃሴ") የተቀነቀነው በትግራይ ላይ ደርሶአል የተባለው የዘር ጭቆና አንደኛው መሰረቱ የጣሊያን እና የእንግሊዝ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ነው። ከትግራይ ውስጥ መገለል ብቻ ሳይሆን እግሩም እጁም የተቆረጠ አይጠፋም። መስረቱ ግን የብሄር ጭቆና ሳይሆን በጣሊያን ወረራ ጊዜ ከጣሊያን ጎን ሆነው ኢትዮጵያን በወጉ ላይ በተሳበጩ አርበኞች ( ህወሃት ነፍጠኛ የሚላቸው እና በአማራነት የከሰሳቸው) የተወሰደ ርምጃ ነበር። ከዚያው ከትግራይም እንዲህ ያደረጉ አርበኞች እንደነበሩ ይነገራል።

የሆነ ሆኖ የዛሬ ህወሓት የወሰደው ርምጃ ሰልፉን ላዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ግቡን የመታ ነው ባይ ነኝ። እርግጥ ነው ሰው ታስሯል። መታሰሩ ሳይሆን ቁም ነገሩ እስከዛሬ ባለን ተሞክሮ ህወሀት ወደ እስር እና እንዲህ ወዳለ ርምጃ የሚገባው ሲባትት እና አለቺኝ የሚላት የበላይነት ድርግም ያለችበት መስሎ ሲሰማው ነው። ስኬት ነው።
 __________________
በዚህ ብሎግ ላይ የሚወጡ ጽሁፎችን  www.borkena.com ማግኘትም ይቻላል። ድህረ-ገጹ በተጨማሪም ወቅታዊ የሆኑ ዓለም ዓቀፍ እና የአፍሪካ ዜናዎችንም ያካፍላል።
  

No comments:

Post a Comment

Blog Archive