Tuesday, April 7, 2009

የዘመናዊነት ልክፍት

የዘመናዊነት ልክፍት

ጦር ጋሻ ጎራዴ ; እንዲሁም ጾም ጸሎት
በነቂስ ወጥተው የተሰለፉበት
ምድረ አበሻ ተኮልኮሎ የከፈለበት -በደም ; ባጥንት
ጎበዝ እንስት ወጣት አዛውንት የሞተበት ; የሞተለት
ድፍረት ;ቀናዒነት ; ፍቅር ;እምነት ተገምደው የሰሩት
ክቡር ማንነት ; ሌላው አንገት ሲደፋ ዘለግ ያልንበት
የኛም ያሁኖቹ እትብት የተቀበረበት ; ያደግንበት
ክቡር ማንነት ...
አሮጌ ነው ብሎ ""የነቃ "" ግልገል ሲሳለቅበት
ማን ያስረዳኝ ግልገሉን እንዳልነካው ልክፍት ?!!

የተሞተው ለመሬቱ ; ላዛውንቱ ; ለህጣኑ -ላላደገው
ለሴቱ ላሮጊቱ ገና ለሚወለደው
ለሚያምኑት ክርስቶስ ሰውን ለማዳን የሞተው ....እንደማያረጀው
ከገባን ማንነትም የእምነት ያህል ነው ማን ሊያስረጀው ?!
እስቲ ይምጣ አዋቂ አፉን ሞልቶ የሚያብራራ
የፈተነም ካለ ማንነት እንደሚያረጂ በቤተ -ሙከራ
ልክፍት እንጂ የሚሉት ""ዘመናዊነት ""
""ነቅቻለሁ "" የሚለውን ግልገል የሚጫወትበት
በውል ያልተጤነ ""ዘመናዊነት ""
ማንነትን መናቅ ; እራስን መጠየፍ አስታቅፎት
ማንነትህ አሮጌ ነው እያስባለ የሚያስወተውት
የሰውን አሽቃብጦ የራሱን ሲሳሳት
ቢቻል ኖሮ መውሰድ ጠበል ሁለት ሰባት
መሞከር ነበረ ቢሆነው መዳኒት ::

አዲስ ነው የሚለው አብዛኛውን ዓለም ድሮ የጨቆነ
በመሳሪያ ብርታት ረግጦ የገዛ ሕዝብን እያፈነ
ጠመንጃ ደብቆ እጂ አዙር ቢያደርገው
""የነቃው "" ግልገሉ አዲስ አደረገው
ግልገሉ እንደሚለው እንዲህ እንዳሁኑ
ምኞትን ደብቀው አገር ገለው ሊከፉኑ
ጦቢያ እናስልጥን ቢሉ ፈቃድ ስጡን
የውነት የነቃው ያ የድሮ ግልገል ...
ፍርጥም በማለት -እኛ የማንን ጐፈሬ እናበጥራለን ?!
ይልቅ አያያዙን አሳዩን እኛስ ምን ሊያቅተን !

ያኔ ገሸሽ ሲል ላሰልጥናችሁ ባይ
ግልገሉም ሲረዳ መሆኑን ቃል አባይ
በል ዓይንህን ላፈር ወደዚህ እንዳታይ !

አሰልጣኝ ቁርጡን ሲያውቅ ዘራፍ አለ አጓራ
ዘራፍ ባይ አላየ የሚወድ ተራራ
በሌላው ዓለም ሲያይ ወራሪ ሲስፋፋ
አበሻንም ወሮ አንገቱን ሊያስደፋ
በጦር አንበርክኮ አበሻ ምድር ሊስፋፋ !

መድፍ ታጥቆ ቢያየው መች ፈራው አበሻ -ፊት ልፊት ...ገጠመ
ዘራፍ ያለው ጨቋኝ እንኳንም ሊጨቁን እራሱ ወደመ
ያበሻም ማንነት በድል ተሽልሞ
ልዩ ታሪክ ሆነ ዓለም አስገርሞ

በውነት የነቃው የተገለጠለት አላስነካም ያለው
የድሮው ግልገል ነው ማንነቱን ወዶ ለዚያ ሲል የሞተው
ይኼ ልክፍታሙ በሰው የሚኮራው
ራሱን ቸርችሮ ላሰልጣኝ የሸጠው ...በዛ የሚያተርፈው
መንተፍረቱም ቀርቶ ክብር ማንነት ""አሮጌ "" እያለ ሚጠራው
እራሱን የማያውቅ የሆነ በዋል ፈሰስ
ጸሐፊው ይለዋል የማንነት ልክስክስ ::

ጥለት ሆኖ ሳይቸግር ጤፍ ብድር
የማያረጀውን የማንነት ጥሪት አሮጌ እያሉ መደናገር
ማንነትን ሸጦ ባልባሌ ነገር
መቸስ ከወደደ እራሱ ይጋተው ሌላውን አያሳክር !!

ለሚያምኑት ክርስቶስ የሞተው እንደማያረጀው
ማንነትም የእምነት ያህል ነው ማነው የሚያስረጀው ?!


ጥቅምት 11, 2001 ዓመተ ምህረት

No comments:

Post a Comment

Blog Archive