Sunday, May 10, 2009

የሰፈሬ እናቶች

የደግነት ድካ
የቸርነት ዋርካ
የሰፈሬ እናቶች
እነኚያ ደጋጎች
የማምላክ ወዳጆች
ምንም ሳይኖራቸው
ዐመል ሆኖባቸው
ለሰፈር ልጃቸው
ይፈታል እጃቸው ::
"" የኔ ልጂ በሞቴ አፈር ስሆንልህ
እንዴት እድርጌ እንደሰራሁት ብታይ እኔ እናትህ
እፈር ስሆንልህ ?!
እንዲያው ምን ሆነህ ነው ትንሽ ብትቀምስ
ጥሩ ድቁስ
እንጀራውም ትኩስ
ቆንጆ ሽሮም አለ ካንጀትህ እንዲደርስ
ምነው ደስ ቢለኝ የልቤ ቢደርስ ?! ""
መስጠት እኮ ነው የልባቸው
ለወደዷቸው ልጆቼ ላሉአቸው !

በጎን ዘንበል ብለው
ዐመዱን ተታከው
"'እፍ "" እያሉ 'ሚያነዱት እሳት
ፊታቸውን እንደጉልቻው ድንጋይ ጠብሶት
ጥላሸት ፊታቸው ላብ ቸፍ ብሎበት
ኑሮ የገደላቸውን 'ረስተውት
ከመጤፍ ሳይቆጥሩት
""አፈር ስሆንልህ ብላልኝ ይሉኛል ""
እኔን እንዲሞቀኝ እንደዛ ጠቋቁረው
ጻዕዳ ፍቅራቸውን ይደርቡልኛል ::
ልክ እንደ ትልቅ ሰው ካንጀት ያከብሩኛል
እንዲህ ያለ ሐገር ;
እንዲህ ያለ ፍቅር ;
እግር እስኪነቃ ሲኬድም ቢታደር
ከወዴት ይገኛል ?!

እንደ አለመታደል
እነዚያን እናቶች
ባይኔ ሳላያቸው
""አረፉ "" ይሉኛል
አንድ ቀን ሳያርፉ
ሲለፉ ላለፉ !

የሰፈሬ እናቶች
እነኚያ ደጋጎች
የማምላክ ወዳጆች
አምላክ ይክፈላቸው
መሬት ይቅለላቸው !!!


በሞት ለተለዪ ሁለት ጎረቤት እናቶች የተቋጠረ

ሚያዚያ 16, 2001 ዓ .ም

No comments:

Post a Comment

Blog Archive