የዛሬ
ሶስት አና አራት ዓመት ይመስለኛል ከአንድ ጓደኛየ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የኑሮ ውድነት በስልክ እያወራን ነበር። የችግሩን
መጠን የገለጸው እንጀራ መብላት በዚህ ዘመን አቅም የሚጠይቅ ነገር አንደሆነ በማስመር ነበር። ያወራነውን ቃል በቃል ባላስታውሰውም “ድሮ እኮ ሰፈር ውስጥ የመጨረሻ ድሃ
የሚባሉት ጤፍ ገዛን ሲሉ ሰምተናል። አስፈጭተው ሲመጡም አይተናል። የአሁኑ አኮ የሚገርም ነው። እንጀራ ብርቅ ሆነ።ጤፍ ገዝቶ ማስፈጨት
አንደዱሮው ደሃውም ጭምር የሚያደርገው ጉዳይ አይደለም። የስኬት ሁሉ መገለጫ እይሆነ ነው ” በሚል መንፈስ በቁጭት አና በእልህ
አንደተናገረ አስታውስሳለሁ። ምን አልባት ይሄ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሁኔታ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለነበራቸው እና የዝቅተኛውን ማህበረሰብ
የኑሮ ሁኔታ በቅርበት ለማያውቁ የማይገባ ነገር ሊሆን ይችላል።
ድህነት
ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከድህነት
ጎዳና እየወጣች ነው ፣ የኢኮኖሚ እድገት አያስመዘገበች ነው(በዚህም ዓመት የስምንት በመቶ እድገት ታሳያለች የሚል ትንቢት ቢጤ
በ'BBC'ም ዜና ሳልሰማ አልቀረሁም) ፣ ከሰላሳ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ
መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገሮች ጎራ ትሰለፋለች አየተባለ ባለበት ጊዜ ቅጥ ያጣ ድህነት መስማት ግራ ያጋባል። ጤፍ መግዛት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ አብዮት አና ተዓምር የሚመስልበት ደረጃ ላይ ተደርሶኣል።አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንዳቅሙ
ጤፍ ይገዛባት የነበረች የኢኮኖሚ አቅሙ እንኳ ከድታዋለች። ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህበረተሰብ ክፍል ያለ ብዙ ጭንቅ አና ስቃይ ሊያገኛቸው
የሚገቡ የዕለት ተዕለት የምግብ ሸቀጦችን ጭምር የወርቅ ዋጋ አንዲኖራቸው የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየተከተሉ ህዳሴ ቢባል ወርቅ
ነን ቢባል ብዙ ትርጉም አይሰጥም።
ኃይለማርያም ደሳለኝ ምን ጨመሩበት?
ግነት።
‘እንደሳቸው’ የጤፍ ዋጋ የተወደደው “አቅርቦት እና ፍላጎት ስላልተመጣጠነ፣
ጤፍ ተጠቅሞ የማያውቀው የህብረተሰብ ክፍል የጤፍ ፍጆታው ስለጨመረ ነው”
ለመሆኑ ጤፍ ቀምሶ የማያውቀው የህበረተሰብ ክፍል ገቢው በምን ያህል እጥፍ ቢያድግ ነው ከስድስት አና ሰባት አመት በፊት
ጀምሮ ወደ ሰማይ እየጓነ የመጣውን የጤፍ ዋጋ የደፈረው? ጤፍስ ለውጭ ገበያ የሚላከው (የሚልከው አላልኩም) ጤፍ ቀምሶ ለማያውቅ
የህብረተሰብ ክፍል ነው? የቅኔ ችሎታቸውን ስለማላውቅ አንጂ አቶ ኃይለማርያም የጤፍ ፍጆታን በተመለከተ ያሉት ነገር “ውስጠ ወይራ
ይሆን?” እንዴ የሚያስብልም ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ጤፍን የመግዛት አቅም ያለው ይብዛም ይነስም በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የኢኮኖሚ
አቅም የፈጠረለት የስርዐቱ የፖለቲካ አፋሽ አጎንባሽ አንደመሆኑ እውነታ ያዘለ ውስጠ ወይራ አነጋገር ሊሆን ይችል ይሆናል።
በሌላ
አንጻር ደሞ በተደጋጋሚ ከሚናገሩት ነገር መውሰድ የሚቻለው ግምት የአቶ ኃይለማርያም ሁናቴ እና “ከለማበት የተጋባበት” የሚለው
እሳቤ የዱባ አና የቅል ያህል ልዮነት አላቸው። አቶ ኃይለማርያም “ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም” በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰው ይመስላሉ። በስንት
ጭቅጭቅ ተዳክሞ አና ተሸንሽኖ የተሰጣቸውን ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ
ከሚያንጸባርቁት ባህሪ መረዳት የሚቻለው ሰውየው አዛዥ ናዛዥ ያለባቸው
ችግራቸው ያልታወቀላቸው እስረኛ ናቸው። ቁርጡ የታወቀው የነ በቀለ
ገርባ አና የነ እስክንድር እስር መሻል ሳይሆን እጂጉን ይበልጣል፤መሰረታዊ በሆነ መልኩ። እነ በቀለ ገርባ ሪዮት አና እስክንድር
ጭቆናን አና ጨቋኝን በመቃወም በሚያምኑበት እና ህጋዊ በሆነ መንገድ
መብታቸውን ለማስከበር ተንቀሳቅሰው የታሰሩ መሆናቸው ከኃይለምርያም
ደሳለኝ የተሻሉ አስረኞች ያደርጋቸው። በእስራቸው፣ በእንግልታቸው ውስጥ ፋይዳ አለ። ብዙ ባንጠቀምበትም። ሰው እምነቱን የፓለቲካም
ይሁን ሌላ አላስነጥቅም ብሎ ከነእምነቱ ሲታሰር ክብሩን ይጨምርለት አንደሆነ ነው አንጂ አይቀንስበትም። በእስሩ ውስጥ ክብሩም አብሮት
አለ። ሰው የሰውነት ክብሩን ለጨቋኞች ከሚያሳየው እምቢተኝነት የበለጠ በምንም ነገር ሊያስመሰክር አይችልም። አነኚህ እስረኞች የራሳቸው
እስረኞች አይደሉም። ባለራዕዮች ናችው። ክብር ያላቸው ናቸው። አንግዲህ
“ይቅርታ ጠይቁ” የሚለው ፈሊጥ የታሳሪው ክብር ከአሳሪው ወገን በልጦ ሲገኝ ያንን ክብር ለማስጣል የሚደርግ ሙከራ መሆኑ ነው።
በተቃራኒው
ደሞ አቶ ኃይለማርያም ጨቋኞችን ደግፈው ከጨቋኖች ወገን ሆነው እየተጨቆኑ ያሉ የህሊና ያልሆነ እና ምንነቱ ያልታወቀላቸው እስረኛ ናቸው። የሚታወቀው ነገር ቢኖር የራሳቸውም የአለቆቻቸውም እስረኛ ናቸው። የእምነት
ጥንካሬ አንኳን ባይኖር ፣ የፖለቲካ ብስለት ባይኖር አነጋገርን ማሳመር ብዙ እውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ አልነበረም። ዮኒቨርሲቲ ውስጥ
አስተምሮ የነበረ ሰው ፣ የዪኒቨርሲቲ ዲን የነበረ ሰው ፣ እድሜው በአርባዎቹ መጨረሻ ያለ ሰው አንደበቱ ሳይንተባተብ ሃሳቡ ሲንተባተብ
ማይት ያውም ጠቅላይ ሚኒስተር የሚል ማዕረግ ተለጥፎለት ለሰሚው ግራ ነው።
የጤፍ
ዋጋ ተወደደ ሲባል በቆሎ መበላት አለበት የሚል ፖለቲከኛ ምን እያለ ነው ያለው? የጤፍን ዋጋ ለመቀየር አቅም የለኝም ማለቱ ነው?
ምንም ማድረግ አልችልም ማለቱ ነው? ኬኒያ እያለሁ የኬኒያን ፓለቲካ በፍቅር እከታተል ነበር። ያኔ የፍትህ ሚኒስተር የነበረው ኪራይቱ ሙሩንጊ በጊዜው
ስለነበረው ረሃብ አስተያየት ሲሰጥ “ኬኒያውያኖች የሚራቡት ምግብ ስለሚመርጡ ነው። ለምሳሌ ፈረስ አንበላም። አህያ አንበላም። ሌሎችንም
እንስሳት[አይጥን ማለቱ ነው ያሉ ነበሩ]አንበላም” ብሎ ነበር። በነገታው የፖለቲካ ካርቱኒስቶች "ኪራይቱ
ስጋ ቤት ፤ የአይጥ ስጋ፣ የአህያ ስጋ እና የፈረስ ስጋ እንሸጣለን” በማለት በ"ዴይሊ ኔሺን" ይሁን በ "ኢስት ስታንዳርድ" ጋዜጣ ላይ ካርቱን
አውጥተው ነበር። ያኔ ኪራይቱ አንደፍትህ ሚኒስተር የነበራቸው ህገ-መንግስታዊ ጉልበት አና የእኛ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም
ደሳለኝ ያላቸው ህገ-መንግስታዊ የፖለቲካ ጉልበት አይገናኝም። ኪራይቱ
ጠንከር ያለ ጉልበት ነበራቸው። ኬኒያ ህገ-መንግስቱ ከወረቀትነት ያለፈ ፋይዳ ስለነበረው። አንደዛም ሆኖ ለህዝቡ ሕገመንግስታዊ
ጉልበት የሚጨምር አና የፖለቲካ ቀውስ አንዳይኖር ይረዳል የተባለለት አዲስ ህገ መንግስት ለማርቀቅ ብዙ ሚሊየን ገንዘብ አውጥተው ባለሙያ ቀጥረው ነበር። የህወሃት/ኢሃዴግ ህገ
መንግስት በርግጥ የማይረባ አንደሆነ በተደጋጋሚ ካረጋገጡት ነገሮች አንዱ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ነው።
ህገ-መንግስቱንም አቶ ኃይለማርያምንም አወቅን። በጌትነት ውስጥ ያለ ባርነት(ያውም የሳቸው ጌትነትም አይመስልም) በባርነት ውስጥ
ካለ ባርነት የከፋ አንደሆነ ተረዳን። አንድምታው ምንድነው? ነው ጥያቄው!
‘ራስን’ መሆን
ራስን
መሆን የሚለው ሃሳብ አንደ ቡድን አባል (የፖለቲካ ቡድን ይሁን ሌላ አይነት) ካየነው በተወሰነ መልኩ ስሜት ላይሰጥ የሚችል ጉዳይ
ነው። ምክንያት- አባል ለመሆን የምንፈልገው ቡድን ግብና ፕሮግራም
ሙሉ በሙሉ በራሳችን ፍላጎት፣ እምነት እና አምሳል የተቀረጸ ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። እንዲህ ባለ ሁኔታ አባል የሚኮንበት ምክንያት ወይ በሂደት ከውስጥ ታግሎ
ነግሮችን ለማስቀየር ነው፤ አሊያም ደሞ ‘ሰጥቶ ለመቀበል’ የሚቻልበት
ሁኔታ ይፈጠራል ከሚል እምነት ነው። ያ ሁኔታ እስከሚፈጠር ድረስ አንደ አባል የምናዋጣው አና ካዋጣነው በኋላ አንደልብ
የማናገኘው ‘ራስ’ አለ። የምናዋጣው ነጻነት አለ። የቡድኑ አባል ሆነን አስከቀጠልን ድረስም አንድናዋጣ የሚጠበቅብን ነጻነት ወይ
‘ራስ’ ባለቤትነቱ ከራስ ወጥቶ የቡድን ይሆናል ማለት ነው።
በምናዋጣው
ነጻነት የሚሰራው ነገር ካዋጣነው ነገር ጋር ፈጽሞ ሳይመጣጠን ሲቀር ቀስ እያለ ወዳላዋጣነውም “ራሳችን” ፣ወዳላዋጣነውም ነጻነታችን
መምጣቱ አይቀርም። የፓለቲካ እንቅስቃሴ አካል ሲኮን በምናዋጣው ነጻነት እገዛ ተጨቋኞች የበለጠ የሚጨቆኑበት ፣የሚጎዱበት ከሆነ ፤ጨቋኞች
ደሞ የበለጠ የሚጠቀሙበት ከሆነ ቆም ብሎ አለማሰብ “ራስን” ከመሳት
ባለፈም የህሊና ክህደት እና ወንጀልም ጭምር ነው። ክሰው በታች የመሆን እና የአለመርባት ማረጋጫ ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ
ውስጥ ሆኖ መተባበር ከጥቅሙ (ጥቅሙ የኢኮኖሚም -ጥቅም የሚባለው እሱ ክሆነ -ወይንም ሌላ ይሁን) ጉዳቱ ያመዝናል። በክርስትና እምነት
“ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነብሱን ግን ቢጎዳት ምን ይጠቀማል” ተብሎ አንደተጻፈው ሰው በህሊናው የከሰረ ቢሆን እና ሌላ ነገር ቢያተርፍ
ምን ይጠቅመዋል?? በህሊናውስ የከሰረ ሰው በምን ተዐምር የፍትህ አርበኛ ሊሆን ይችላል? በምን ተዐምር የሃገር ተስፋ አና ለሃገር
የሚቆረቆር ዜጋ ሊሆን ይችላል? ምክንያት እየደረደረ የከዳውን ህሊናውን ከሚሸነግል በስተቀር?
አቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ በሰሞኑ የፓርላማ ውሎ፣ከዛም በፊት በነበሩ ውሎአቸው ራሳቸውን ያልሆኑ ሰው አንደሆኑ በገሃድ አሳይተዋል። በአቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ ቤት ምናልባት “ራሳቸውን ሆነዋል” ። የኃይለማርያም
ደሳለኝን መለሳዊ ስብዕና ኃይለማርያም ደሳለኝ ላይ ብቻ የሚያቆም ጉዳይ ቢሆን አንደችግር ባላየሁት። ችግር የሚሆነው የሚተካው ትውልድ የአቶ ኃይለማርያም ዓይነት (አንደሳቸው የሚብስበት ባይመስለኝም) የረዥም
ጊዜ እሴት አና ማንነት ያለው ህዝብ ውጤት መሆኑ ቀርቶ የግለሰብ
ቅጂ የሆነ አንደሆነ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሚከተለው ፖሊሲ እና ፖሊሲው የሚፈጥራቸውን ውጥንቅጦች ቢያንስ
በማህበራዊ ደረጃ የምናመክንበት አካሄድ በሌለበት ሁኔታ የአቶ ኃይለማርያም አይነት ትውልድ አንደማይፈጠርስ አንዴት መተማመን ይቻላል?
አንደሚመስለኝ
የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስብዕና አና እይታ ከብዙ ኢትዮጵያውያን ጋር ይጋጭ የነበረበት ምክንያት ሟቹ “ራሳቸውን የሆኑ” እየመሰላቸው
ከየቦታው ያግበሰበሱት አና አንዳንዱም በውል ያልገባችው የሚመስል አስተሳሰብ ነበር። በነፍጠኛነት አና በጠላትነት ፈርጀውት የነበረው
ህዝብ ላይ የነበራቸው እይታ ለዚህ አንደ ምሳሌ የሚሆን ይመስለኛል። ማንን አነበቡ? ከማን ጋር ተወያዮ? በምን አይነት ሃሳብ አቅጣጫ
ተጓዙ? የሚሉት ጥያቄዎች ለታሪክ ተንታኞች ተትተው ያንን ከየቦታው አግበስብሰው በሰሩት የራሳቸው በመሰላቸው “ራስ እና ስብዕና”
ጓደኞቻቸውን አስተባብረው በማህበራዊ አስተሳሰባችን ያደረሱትን ውድመት የሚገባን ዛሬ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያዊ ከወደምን በኃላ
ነው። እየወደምንም ነው።
ከዚሁ
“ራስን” ከመሆን ሃሳብ ጋር በተያያዘ በሌላ አንጻር የተለያየ ጉዳይ
ይዘው የ’አክቲቪዝም’ ስራ እየሰሩ ያሉ ወጣቶች ከያዙት ጉዳይ ባለፈም “ራሴን ነኝ። ራሴን ነው የምሆነው” አይነት ዜማ ሲያዘወትሩ ወደ ማህበራዊ ግንኙነት ሲቀላቅሉ ይስተዋላል። መጀመሪያ
ነገር “ራስን መሆን” ከማህበራዊነት ጋር አይንና አፈር (ፈረንጆቹ oxymoron እንደሚሉት ያለ) ነው። ሲቀጥል ደሞ “ራሴ” በሚሉት
ባህሪ የሚንጸባረቀው ሃሳብ ሲገመገም ምንጩ ራስ ሳይሆን ባህር ማዶ ሆኖ ይገኛል።
በዓለማችን
ራሳቸውን ሆነው የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ህዝቦች አሉ። ከታሪክ አንደምንረዳው ኢትዮጵያውያንም ራሳቸውን ለመሆን የከፈሉትን ዋጋ
ቀላል አልነበረም። በትክክለኛው ራስን መሆን ስህተት አይደለም። ቅንጦትም አይደለም። የእድገት ፍላጎት አለመኖርንም አይጠቁምም።
ይልቁንም ኮለል ካለ የነጻነት ግንዛቤ የሚመጣ ባህሪ ይመስላል። እርግጥ
ነው አንዲህ ያለው “ራስን” መሆን በውስጡ ያለው ጠንከር ያለ ማህበራዊነት
ስለሆነ ለእድገት ውሃ ልክ እንደሚሆን ይሰማኛል።
የተጋረጠው
ችግር ይሄንን ያለመመርመር ነው። የተጋረጠው ችግር ጌትነት በሚመስል ባርነት ውስጥ የሚታየው መመቻቸት ነው። ከውስጥ አንደ ኃይለማርያም
ደሳለኝ አይነት ራሱን የካደ የአንድ ግለሰብን ስብዕና እንደ ሃይማኖታዊ እውነት የተቀበለ ካለ፤ ከውጪ ደሞ በሌላ አይነት ‘ጌትነት’
ውስጥ ያሉ የሚመስላቸው “ራሴን ነኝ” የሚሉ የሌላ ስሪቶች
ካሉ የህዝባችን አና የሃገራችን ዕጣ ፋንታ መመለሻ ወደሌለው ባርነት ከመትመም ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ምናልባት ይሄኛው ትውልድ
ነገሩን አውቆት፤ በባርነቱ አምኖበት ይሆናል። እንዴት በሚመጣው ትውልድ ይፈረድበታል??! የሃገር ቀጣይነት እና ተስፋውስ ምንድን
ነው?