Monday, August 27, 2012

“የጠሚው” ሞት ፣ “ሕዝባዊ ለቅሶ” አና ማህበራዊ አንድምታው


ከአንድ ወር በፊት የ"ጠሚው" መሞት በውጭ ሃገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ጊዜ የህወሃት አመራር ጉዳዮን በሚስጥር ይዞ ሃዘኑን እይጨረሰ ፤ በጎን ደሞ"ጠሚው" ሞቶአል የሚለውን ዜና አያስተባበሉ( በዓለም አቀፉም ማህበረሰብ ለዜናው መታፈን ተባባሪ ነበር) የስልጣን "ዝውውር" ላይ አየሰሩ ነበር። በሚቆጣጠሯቸው አና በአነሱ ቀጥተኛ አና ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኖ ስር ባሉ መገናኛ ብዙሃም ስለ “መተካካት” አና ከመለስ ዜናዊ በኋላ ስለሚሆን የፖለቲካ ሁነት ለውይይት በማቅረብ ህዝቡን ለሃዘን ማዘጋጀት የሚመስል ስራ ሲሰሩ ቆዮ። ካድሬውም ሳይነገረው ነገሩ አንዲገባው ተደርጎ ለሃዘን ሲዘጋጂ ከረመ። ከዚያ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ከወር በፊት የሞተውን ሰው በ"ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዮ" ተብሎ ድራማው በጧት በቴሌቭዥን በቀጥታ መተላለፍ ጀመረ።

በለቅሶውም ላይ ባለስልጣናቱ ተኮልኩልው አብረው ሲተውኑ አየን። አምስት ሚሊየን ደርሶአል የተባለውም የህወሃት/ኢሃዴግ አባል የድራማው ተዋናይ ሆነ። በቤታቸው ጊቢ ድንኳን ካስተከሉ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስከ ድንኳን የሚጥሉ መንደርተኞች አንዳሉ ተሰማ። በየቀበሌው ሃዘነተኛው የሚፈርምበት አና የ”ሰዐት ፊርማ” የሚመስል መዝገብ አንደተዘጋጀ፤ ይባስ ብሎም በውጪ ሃገራት ዘመድ ወዳጂ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለዘመድ ወዳጆቻቸው ስልክ አየደወሉ የጠሚውን ከዚህ ዓለም [ከነበሩበት የራሳቸው ዓለምም] በሞት መለየት አንዲያረዱ ማሰሰቢያ ቢጤም ተላለፈ። ማሳሰቢያውን ተቀብለው የደወሉም አልጠፉም። በኢትዮጵያ ባህል ሰው ሲሞት አለመወቀስ ብቻ ሳይሆን ያልነበረውን አና ያላደረገው ጭምር ገጽታ ማላበስ አና መካብ አንግዳ ነገር ባይሆንም፤ ጠሚው ከሞቱ በኋላ ስለ ጠሚው የተፈጠረው ስብዕና ከመጋነንም ባለፈ ከእውነት ጋር አይን አና አፈር የሆነ ጉዳይ ሆኖ ተገኘ። የውሸት ገበያው ግን የደራ ነበር።

በተቃዋሚ ፓርቲዎች አና በተቃዋሚ አስተሳሰብ ላይ የነበራቸው “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ፓሊሲ፤ ለውጭ ቱጃሮች ባልባሌ ዋጋ የተሸጠው መሬት አና ዜጎች በሃገራቸው ወደፊት የሚጠብቃቸው ዕጣ ኣቅመ ቢስ ገባርነት “የሆነበት ሁኔታ”፤ ሳይገባው ሶማሊያ ተልኮ ሞቶ መሬት ለመሬት የተጎተተው አና ሟቹ ጠሚ "የሞተው የቆሰለው ምናምን ያለውን ዝርዝር የመናገር ግዴታ የለብኝም"ብለው በፓርላማ ያላገጡበት ሰራዊት አና የሰራዊቱ ወገን፤"መቸ አንደምለቃችሁ አልነግራችሁም። ጸሎት አድርጉ" ተብሎ የተፌዘበት ሕዝብ፤ በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ፣በኦጋዴን፣በአዋሳ፣በጎንደር አና በተለያዮ የሃገሪቱ ክፍሎች የተጨፈጨፉ አና ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ፤ የመናገር አና የመጻፍ ነጻነታቸውን ብቻ ስለተጠቀሙበት በገፍ በየእስር ቤቱ የተጣሉ አና ለመግለጽ የሚዘገንን አካላዊ ድብደባ የደረሰባቸው ወገኖች ተረስተው፤ ይህን ሁሉ ጉዳይ አድራጊ ፈጣሪ በመሆን ያቀናበሩአና የመሩ አንድ ትምክህተኛ አና ሲበዛ ዘረኛ ግለሰብ ሲሞቱ “አንበሳው፣ ጀግናው፣ አስተዋዮ” አየተባለ ሲነገር መስማት አና ማየት አጂግ በጣም ይገርማል/ይገማልም። ጉዳዮን አሳዛኝ የሚያደርገው በድንፈ ሃሳብ ደረጃ ሃገር ተረካቢ ነው የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል -ወጣቱ -በሰውየው የአመራር ዘመን የተፈጠረውን ብልሹ ፣ በዘር ላይ የተመሰረተ እና ሙሰኛ አስተዳደር ፈጽሞ ረስቶ አብሮ ሃዘነተኛ ሲሆን ማየቱ ነው። አንደ ፓለቲካ ስልጣን ማቆያ ስትራቴጂ በተየያዮ የሃገሪቱ ክፍሎች ያስጫሩት የጎሳ አና የሃይማኖት ግጪት አና ግጭቱ ያስከተለው የህይወት መጥፋት አና ስደት ተረስቶ አስተዋይ መሪ ናቸው ተባሉ። ህወሃት ስልጣን ይዞ ካልቆየ ሃገሪቱ ትበታተናለች አያሉ ሲደነፋ የነበሩ ሰው አንደ አስተዋይ አና ለኢትዮጵያ አሳቢ መሪ ተደርጎ ተሳለ።የኢትዮጵያ መተንፈሻ ሳንባ አና ኢትዮጵያ የተንጠለጠለችው በሱ ላይ እስኪመስለን ድረስ ለማመን የሚያስቸግር እየየ ሰማን። ሀዘን በፓለቲካ ቅስቀሳ ዘመቻ መልክ ሲቀናበር የትኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚያቀርበው ለቅሶ እና እየየ አውነት ሊመስል አንደሚችል ግምት ውስጥ አንኳን ሳይገባ የሚበሉት የሌላቸው በጎዳና የሚተዳደሩ ፣የኔቢጤውች፣ “ማርሽ ለቃሚዎች” ሳይቀሩ የጠሚው መሞት በመፃዒ ዕድላቸው ላይ የሚያስከትለው እክል ያለ ይመስል አና ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት ስርዐት ተጠቃሚ የነበሩ ይመስል መሪር ሃዘነተኞ ሆነው የድራማው አካል ተደረጉ።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን ልማት አንቀጥላለን” የሚለውን መፈክር መስተጋባት ተጀመረ።ነገር ግን ህወሃት ሃዘን ላይ ነኝ ብሎ ህዝቡን አያደናቆረ መሪር ሃዘነተኛ ለማስመሰል በሚተጋበት በዚህ ሰዓት እንኳ አሁንም ዜጎች ግፍና ሰቆቃ አየተፈጸመባቸው ነው። ትላንት ተመስገን ደሳለኝ ከሰው ጋር አንዳይገናኝ ሆኖ ወደ እስር ቤት ተወርውሮአል። ባነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ባለቻቸው ትንሽ ግሮሰሪ መጠጥ ለመሽጥ ሙዚቃ ከፍታችኋል ተብለው እንደተደበደቡ አና ቤታቸው እንደተዘጋባቸው አየሰማን ነው። የተፈጠረው ሁኔታ ህወሃት ከተጠቀመበት ከህዝብ ጋር ሊታረቅበት ይችላል ከሚለው መላምት በተቃራኒ ሁኔታውን ተጠቅሞ አፈናውን ለማጠናከር ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። ብአዴን፣ ኦህዴድ አና ሌሎቹ ደሞ መለስ አንድ ወቅት ፓርላማ ላይ አንደተናገረው "ወባ አንደያዘው ሲንቀጠቀጡ" እየታዮ ነው። የያዛቸው ግን ህወሃት ነው። የብአዴን፣ የኦህዴድ አና የደህዴን መንቀጥቀጥ ታች ወዳለው ሰባት ሚሊየን ደርሶኣል ወደሚባለው ኣባል ወርዶ ፤የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍላ ላይም ስለተጋባ ነው እየየ ሲቀልጥ የሰማንበት ምክንያት ። ችግሩ ያለው ከላይ ሆነው ደህንነቱን አየተቆጣጠሩ ባሉት ሰዎች አይደለም።ከታች ተሸክመውት ያሉት የብአዴን፣የኦህዴድ አና የደህዴግ አባላት ናቸው። ለመሆኑ የጠሚውን አስከሬን ይጠብቁ ከነበሩ የህውሀት የጦር መኮንኖች ምን አነበባችሁ? ከሳሞራ አና ብአዴን መሪዎች --በተለይ ከአዲሱ ምን አነበባችሁ? ፖለቲካዊ ከሚመስለው የአዜብ ለቅሶ ጀርባ ምን ግምት ወሰዳችሁ? ጠሚው- መለስ ዜናዊ- ሲወጡ አና ሲገቡ - “ዞር በል ፣ተኛ ፣ጥፋ” እየተበለ ቁም ስቅሉን ሲያይ የነበረ ሕዝብስ ዛሬ የአስከሬናቸውን ሳጥን በግላጭ ታቅፎ “መሪር”ህዘነተኛ ሲሆን ምን ተሰማችሁ? የሰፈሮቹን ልጆች፣ጓደኞቹን አና ወገኑን በቀጭን ትዕዛዝ በሞት ያስነጠቁት ሰው ሞተው ሲያቸው “ለፍርድ ሳይቀርቡ የሚል” ቁጭት ቀርቶ ጭራሽ በሞታቸው መሪር ሃዘነተኛ ሲሆን ምን ተሳማችሁ? የጎሳ ፓለቲካ ቀንደኛ ተቃዋሚ ሊሆን የሚገባው አዲስ አበቤ የጎሳ ፓለቲካ ግንባር ቀደም አርክቴክት ሲሞት ያቀለጠው እየየ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት ዘመናቸው ባደረሱት ጥፋት አና መጠነ ሰፊ ግድያ ምክንያት ለፍርድ ሳይቀርቡ በ”ተፈጥሮ” ሞት መነጠቃቸው ያሳዘነኝን ያህል፤ ከሟች ወገን መሆን የነበረበት ህዝብ ለገዳይ ሲያለቅስ መስተዋሉ ከዛ የበለጠ አሳዝኖኛል።

በፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዘመን የፋሽስቶቹ የጎሳ ፓለቲካ በገሃድ የተሽነፈው አዲስ አበባ ነበር። በፋሺስቶቹ የመንፈስ ልጆች በህወሃቶች ጊዜ ነገሩ ተገላበጠ -ምንም አንኳን በዘጠና ሰባት ሌላ ታሪክ ታይቶ የነበረ ቢሆንም። በዘጠና ሰባት በሁለት መልኩ የጥሊያንኑን ወረር የሚያስታውስ ነገር አንደተፈጠረ አይዘነጋም። የፋሽስቶቹ የመንፈስ ልጆች አንደ ፋሺስቶቹ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈዋል። ኢትዮጵያውያኑም በባዶ አጃቸው ከባለ መትረየስ ጋር እየተፋለሙ አንደ አባቶቻቸው በአርበኝነት ወድቀዋል። በዘጠና ሰባት።ፍትሃዊ ነበሩ ኣልነበሩም የሚለውም ነገር ሌላ ጉዳይ ሆኖ (ስለማያስፈልግ) በአምባገነንነት መመዘኛ ከመለስ ጋር ስናወዳድራቸው ቅዱስ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት አጼ ኃይለስላሴ ከዙፋን ወርደው በመኪና ወደ አስር ቤት ሲወሰዱ "ሌባ" አየተባሉ የተሰደቡበት አዲስ አበባ ላይ፤ ዛሬ የምር ሌባ አና አራጂ የነበሩ ሰው ማንም ሳይነካቸው በአምላክ ቸርነት ሲያልፉ የከተማው ህዝብ ድንኳን ተክሎ አንጥፎ የሚቀመጥበት ዘመን ላይ ተደርሶል። ኢትዮጵያን ሊለውጥ የማይችል የትምህርት ፓሊሲ አንዴት በድፍረት ትውልድ ላይ ይሞከራል ሲባል፤ “ትምርህት መድሃኒት አይደለም። በአይጥ አይሞክርም ።በሰው ነው የሚሞከረው” ያለው ሰውየ የራሱን ልጂ ሳንፎርድ አና አንግሊዝ አገር ልኮ ዋጋው የማይቀመስ ውድ ትምህርት ቤት ነው ያስተማረው። ዛሬ ሌባ መባሉ ቀርቶለት --- “ለአኔ ማለት የማያውቁ፣ ራሳቸውን የማይወዱ” የሚል ውዳሴ ተዥጎደጎደላቸው። ስለ ባንዲራ፣ስለ ሃገር፣ ስለታሪካዊ ቅርስ አና ባለቤትነት ፣ስለ ህጋዊነት አና ህገ መንግስት ስለ ነጻነት አና ዜግነት የተቀባጠረው አላዋቂ አና በንቀት የተሞላ ነገር ባንዴ ተረስቶ “ኢትዮጵያ በመቶ ዓመት የማታገኛቸው አስተዋይ መሪ ነበሩ” ተባለ። “ወርቅ ነው” ላሉት ህዝብ አብሮአቸው የታገለው አቶ ስየ አብርሃ ከሃወሃት አስባረውት፤ አሱም ህወሃት ውስጥ የፖለቲካ መቆሚያ (ግራውንድ) ሲያጣ ከሌሎች ጋር አሰራለሁ ብሎ ሌላ አይነት ፓለቲካ ሲጀመር ለአቶ መለስ ከ”ወርቅነት” ወርዶ “አህያ” ሆኖ አንደታያቸው ፍንጭ የሰጡት ለምን (ከመድረክ)ከስየ ጋር አትደራደሩም የሚል አይነት ጥያቄ ሲቀርብላቸው “አንኳን ከሰው ጋር ከአህያም ጋር መነጋገር ይቻላል” ብለው ሲወርፉት ነው--ኣስተዋዮ መሪ! በህወሃት በአህያነት የተፈረጀው ግን “ወርቅነቱን” የተወው አቶ ስየን ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ የህወሃትን ባህሪ ጠንቅቆ ካለማወቅ የመጣ የተሳሳት ግምት ነው። ዛሬ በተቀናበረ ሁኔታ አያዘነ የሚመስለው የአዲስ አበባን ነዋሪ ነገ በትምክህት የተወጠረው ህወህት “አህያነቱን አስመሰከረ። እንደ አህያ አየረገጥል ልንገዛው የምንችለው ህዝብ ነው” ብሎ ቢያስብ ማን ጠያቂ አለው? ብአዴን? ኦህዴድ? ደህዴን? ማነው ጠያቂው? በዚህ ሰዐትስ ተመስገንን እስር ቤት መወርወር ስለተሰማቸው አና ሊሰማቸው ስለሚችለው ነገር የሚለው የለም?? የዘጠና አንዱ ጭፍጨፋ ሳይጨመር “ጠሚው” ብዙ ህዝብ ባስጨፈፉበት ከተማ ሰባት ዓመት በማይሆን ጊዜ ያ ሁሉ ሰቆቃ ተረስቶ አንዴት አንዴት ለማመን የሚያስቸግር የጻድቅነት ትክለ ስብዕና ተፈጠረላቸው? አንዴትስ ሰው አምኖ ተቀበለው? ፊት ለፊት የሚታዮ ናቸው የምላቸውን ሁለት ሶስት ምክንያቶችን መጥቀስ እፈልጋለሁ።

በአንደኛ ደረጃ አንደምክንያት የማስቀምጠው የማህበራው አስተሳሰብ ኪሳራን ነው። ኪሳራ የሚለው አገላለጽ ያለምንም ጥያቄ የሚያስማማ(ኦብጀክቲቭ) ላይሆን ይችላል። ለነገሩ ቁጥር አንደ ፊደል ሳይገድል አይቀርም። ለአኔ የሃሳብ ጥንካሬ አና ድክመት የሚሰፈረው ሃሳቡን በሚቀበለው ሰው ቁጥር መብዛት አና ማነስ አይደለም- ምንም አንኳን ያለው ልማድ አንደዚያ ቢሆንም። የማህበራዊ አስተሳሰብ ኪሳራ ስል- የትኛው ነው የከሰረው ማህበራዊ አስተሳሰብ? አንዴት ከሰረ ? የሚል ጥያቄም መነሳቱ አይቀርም። የክሰረውም ሳይሆን ምናልባት የክሰረ የሚመስለው ቢባል ይሻላል።ምክንያቱም የከስረ የሚመስለው ሃሳብ በማይናወጥ ሁኔታ ቁጥራቸው ቢያንስም የተወሰኑ ሰዎች ጋር በጽናት ካለ ከስሮኣል ማለት አይቻልም። ለዘመናት በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተከፈሉበት ታሪካዊ መሰረት፣ከፍትህ ጋር የተያያዘ አና ሃገራዊ ፋይዳ ያለው አስተሳሰብ ይቅር አና በበታችነት ስሜት የተፈጠረ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ምንም አይነት ትስስር የሌለው ጥቂት ሰዎች ጫካ የወሰዱት ሃሳብ አንኳን ከጊዜ በኋላ “አሸንፎ” አይተናል። በትክክል “አሸንፎአል” ወይ ሌላ ጥያቄ ነው። ከአስራሰባት ዓመት የጫካ ትግል በኋላ አየዘለሉ በሚያሳዮት “የአሸናፊነት” ስሜት ጎን ለጎን ኮሽ ስሊልም ኮሽ ሳይልም አንደሰረቀ ሰው አየደነገጡ በድንጋጤ የሚያስሩበት አና የሚገድሉበትንም ሁኔታ አስተውለናል።ለመዝለሉ ይዘላሉ አንጂ ሁኔታቸው ያሸነፈ አይነት ሰው አይደለም። ከስጋት ጋር የሚኖሩ ሰዎች አንድሆኑ የሚያሳዮት ባህሪ ምስክር ነው። በመሳሪያ የነገሰ አና በመሳሪያ የሚጠበቅ የፓለቲካ አስተስሰብ “የአምቧይ ካብ” አንጂ አሸናፊም ሊሆን አይችላም። ያውም “ከአምቧይ ካብ” ባያንስ ነው?!

ዛሬ የከሰረ የሚመስለው የድሮው ማህበራዊ አስተሳሰብ ነው። ድሮ በድህነት ንቅንቅ የማይል ህሊና አና ያገር ፍቅር ገዢ አስተሳሰብ አና የአኗኗር ዘይቤ የነበረውን ያህል ፤ ዛሬ የተፈጠረው ቅጥ ያጣ የኑሮ ውድነት ያንን ያስተሳሰብ መሰረት አንዲንድ አና ድህነት የፖለቲካዊ ዋጋ አንዲኖረው ተደርጎ ስለተፈጠረ፤ “ጠላታችን ድህነት ነው” ከሚለው መፈክር ጎን ለጎን በውስጠ ታዋቂ ለድሃ ሕዝብ ለህሊና መኖር የመቀናጣት ፤ከዚያም አልፎ የአብደት ያህል ሆኖ አንዲታይ ሁሉ ሆነ። በኢትዮጵያ ማህበራዊ ጉዳይ በሚመስሉ ነገር ግን ፓለቲካዊ ፋይዳም ሊኖራቸው በሚችል (ማጤን ለሚፈልግ) ኣዳዲስ የፊልም ስራዎች ላይ በተደጋጋሚ የማየው መልዕክት ይሄንኑ ነው -በቅርቡ ያየሁትን “7ኛው ሰው” ጨምሮ። የመለስ ዜናዊ ለቅሶ ደሞ ያለውን ማህበራዊ ያስተሳሰብ ኪሳራ ቁልጭ አድርጎ በገሃድ አሳይቶኛል። የማህበራዊ ኪሳራውስ አንዴት ተፈጠረ?

ከህወሃት ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ በተለይም ከምርጫ ዘጠና ሰባት ወደዚህ በፊት የነበረው አስተሳሰብ አክሳሪ አና ኋላ ቀርም ጭምር ተደርጎ አንዲሳል ተደረገ። አንደዚህ አይነቱን ድባብ ለመፍጠር “ህጋዊ” ፣ፖለቲካዊ አና ወታደራዊም ርምጃም ተውሰዶኣል። ለህሊና መኖርን አንደቅንጦት የሚያይ አዲስ ማህበራዊ አስተሳሰብ አንደተፈተረው ሁሉ፤ ህሊናን አሳልፎ በመሸጥ የሚገኝ ተቀባይነት አና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንደ ብልህነት ፣ጨዋነት አና አዋቂነት ጭምር አንዲታይ ተደርጎአል። ላልገባቸው ሃሳብ ለማጨብጨብ አና ዘብ ለመቆም አይናቸውን የማያሹ አና ከጭብጨባቸው አና ድጋፋቸው በተለያየ መልኩ መጠቀም የሚፈልጉ- የህሊናን የፍርድ ደውል አና የህሊናን ተቃውሞ የመስማት ብቃት የሌላቸው -‘ንቃተ-ድንቁርና’ ውስጥ ያሉ ብያቸዋለሁ- የሚያሾሙበት አና የሚሸለሙበት ሁኔታ ተፈጠረ(ወይንም ድሮም አንዲህ አይነት ነገር አይጠፋም ቢባል በተለየ ሁኔታ በህወህት አስተዳደር ተስፋፋ።) ንቃተ-ድንቁሩና አና ንቃተ-ደናቁርነት አትራፊ መስሎ የሚታይበት ሁኔታ በአኗኗር ዘየ አና በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መልክም ጭምር አየተስተጋባ ፤ጎን ለጎን ደሞ ንቃተ ህሊና የሚፈጥረው ትግል፣ያገር ፍቅር አና ፈሪሃ ህሊና (በእምነቴ ፈሪሃ እግዚያብሄር ወደምለው ይጠጋል) በግፍ አና በበደል በስቃይ አንዲንገላታ አና በአሳር “ዋ!” አስብሎ ሌሎች አንዳይሞክሩት መቀጣጫ ማድረግም በሰፊው የተሰራበት ጉዳይ ነው። ትግሉ በንቃተ-ደናቁርና አና በንቃት ህሊና መካከል ነው። ንቃተ ደናቁርትነት ያሸልማል። ያሾማል። ንቃተ ህሊና አና ለህሊና መኖር ደሞ ያስቀጣል። አስከሞት።

ንቃተ ህሊና ክቡር ነው። ንቃተ ህሊና አና ለዚያ መኖርም በገንዘብ የማይተመን አና ዋጋው እስከ ህይወት የሚደርስበትም ምክንያቱ ይሄው ነው። በሸቀጥ ገበያ አንደሚታየው- ጥሩ የሚባል ሸቀጥ -በመልኩ፣ በጥንካሬው ፣አምራቾቹ በየዕለቱ በሚነዙት የማስታወቂያ ጋጋታ አና ተጠቃሚዎቹ ባላቸው “ማህበራዊ አና ኢኮኖሚያዊ” ደረጃ ምክንያት በተጽዕኖ አንደሚፈጥሩት የዋጋ ውድነት ሳይሆን፤በተለየ ሁኔታ አና በንቃተ-ደናቁርት ዓለም ለሚኖሩ በማይገባ መልኩ ለህሊና መኖር ዋጋው ከፍተኛ ነው። ህሊና ክቡር ነገር አንደመሆኑ ለህሊና ለመኖር በማይቻልበት ድባብ አና ሁኔታ ለህሊና መኖር ሲባል የሚክፈለው ዋጋ አንደህሊና ውድ ነው። ክቡር ነው። አራሱን የሚያከብር ሰውነቱን የሚያከብር ይከፍለዋል። አንድ ሰው ለህሊናው ሲኖርም የሚኖረው ለራሱ ብቻ አንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል! ማህበራዊ አና ሃገራዊ ፋይዳ አለው ማየት ለቻለ። ውሎ አድሮ ተጽዕኖ ማድረሱ አይቀርም። ንቃተ-ደናቁርትነት ደሞ ርካሽ ነው። የሚሸጥ የሚለወጥም ነው። ለህይወት ከመስጋት ጋር በተያያዘ ይሁን፤ የኢኮኖሚ ጥቅም በማሳድድ ይሁን በጎሳ ታማኝነት ይሁን --ርካሽ ነው። ንቃተ ደናቁርትነት ክቡር ህሊና ስለማይጠይቅ የከበረ ዋጋ አያስከፍልም። ለመጥፎውም ለጥሩውም ነገር እሽታ አና ማስመሰል ብቻ ነው የሚጠይቀው። ንቃተ-ደናቁርትነት አዙሮ የማያይ አና የማስብ አቅሙ እክል ላይ የወደቀበት ሰው ብቻ የሚኖረው የህይወት ዘየ ነው። ንቃተ-ደናቁርትነት በአስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ወይንም በድፍረት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ሳይሆን በመንፈሳዊው ዓለም “ስጋዊ ፍላጎት” በሚባሉ ነገሮች ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ አና ያኗኗር ዘይቤ ነው። “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነብሱን ግን ቢጎዳት ምን ይጠቅመዋል?” የሚለው የክርስቶስ ትምህርት ሁሌ ይሄንን ነጥብ ያስታውሰኛል።

ንቃተ ደናቁርትነት ድህነት የሚወልደው ነገር አይደለም። ኑሮአቸውን ያሸነፉ፣ከማሸነፍም አልፈው “መዋለ-ንዋይ አፍሳሺ” የሚባሉት ሰሞኑን ተሰልፈው ለመለስ ዜናዊ ሲያለቅሱ አይተናል። አርቲስት ናቸው ከሚባሉት አስከ ዓለም ዓቀፍ አትሌቶች ኃይሌ ገብረስላሴ ድረስ። ንቃተ-ህሊና ያላቸው ለእምነት አና ለእውነት የሚኖሩ አየተሳደዱ አና አየተንግላቱ ንቃተ ደናቁሮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆኑ ንቃተ-ድንቁርና የመደርጀት አጋጣሚ ሊያገኝ አንደሚችል አንድና ሁለት የለውም። በማበራዊ አስተሳሰባቸው ሊከበሩ የማይገባቸውን “ተፅዕኖ ፈጣሪዎች” ዕውቅና አና አክብሮት አየሰጠን በሄድን ቁጥር ንቃተ-ደናቁርትነት አየተደላደለ መሰረት አየያዘ ይሄዳል። ሼክ አላሙዲን ያላቸውን ሃብት ተጠቅመው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የንግድ ተቋማትን ኣስፋፍተዋል። የት ላይ አንደሆነ በውል ባላስታውስም አንዴ የሆነ ቦታ አንዳነበብኩት አንደ አዶላ ወርቅ ካለው ኢንቬስትመንት ለኢንቨስትመንት ያወጡትን ገንዘብ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ መልሰው የዛኑ ያህል አንዳተረፉ ተጠቁሟል። አንዲህ ከሚዝቁት ትርፍ ላይ ብዙ ቁምነገር ሊገባ የማይችል (ካላቸው ሃብት አንጻር) በስጦታ መልክ ስለሚወረውሩ ብቻ ባለጠግነትን የህሊና መሸፈኛ መጋረጃ አንደሆነ ነገር በሚያሳብቅ መልኩ ባለሀብቱ ለማህበራዊ አስተሳሰባችን መክሰር ያበረከቱት ቀላል የማይባል አስተዋጾ ተረስቶ ሼሁ ደግ ናቸው አየተባለ ሲወራ የሰማሁበት አጋጣሚ ብዙ ነው። የዕድሜ ባለጸጋ ሊባል የሚችል ሰው ገንዘብ ሳላለው ብቻ ከአንድ ፍሬ ልጂ ጋር መለኪያ ጨብጦ እሽክትር ሲመታ ከእስልምናውም ከኢትዮጵያዊነቱም ጋር ሊጋጨው የሚገባ ባህሪ ባይሆን (በ”ግለሰብ መብት” ሂሳብ) አንኳን አንዲህ ያለው ባህሪ ተረስቶ አክብሮት ባልተቸረው ነበር። ማህበራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የልብ ልብ ሰጥቶት በፓለቲካውም አንጻር የሞከረው ነገርም ግምት ውስጥ መግባት አለበት። ውጪ ያለውን ማህበረሰብ ለህወሃት ፓለቲካ ትርፍ ሲባል በገንዘብ ለመግዛት ያማረው ሰው ነው። ኢትዮጳያ ውስጥ የተሳካው ድሆችን ለፓለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ የማድረጉ አካሄድ ግን ውጭ ሃገር ሊሰራ አልቻለም። ለነገሩ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ በመነሳት ድህነት አሁን ኢትዮጵያ አንደሚታየው ቅጥ ሲያጣ የሚኖረው ፖለቲካዊ ፋይዳ ህወሃት ለራሱ የፈጠረውን አይነት የፖለቲካ ፋይዳ መሆን አልነበረበትም። ከመንግስት ይልቅ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ከፍተኛ የፖለቲካ ምንዛሬ ሊኖረው በተገባ ነበር።

ኑሮን ለማሸነፍ፤ ኑሮን ከማሸነፍ ባለፈም “ጥሩ ኑሮ” (“ቤተር ላይፍ”) ለመምራት ሲባል ለማያምኑበት የፓለቲካ አስተሳሰብ ከማጨብጨብ ያለፈ ትጋት የሚጠይቅበት ሁኔታ ይኖራል። የንቃተ-ደናቁርትነት ደመኛ መስሎ የሚታየው የንቃተ-ህሊና ባለሃብቶች ለህሊናቸው የሚኖሩ አንደመሆናቸው(የማይኖሩ ካሉ ንቃተ-ህሊና አባካኞች ስለሆኑ አነሱን አይጨምርም) ፤ለህሊናችው የሚኖሩ ሰወችን ማሳደድ አና ቁም ስቅል ማሳየት፣ማፈን፣ማንገላታት፣ማሰር፣ማሳሰር አና ማሳደድ ከንቃተ-ደናቁርት የሚጠበቁ የንቃተ-ደናቁርትነት ብቃት መለኪያዎች ናቸው። ኑሮን በወንጀል አና በህሊና ሽያጭ ማሸነፍ ወይንም የተሻለ ማድረግ በስተመጨረሻ ያዋጣል ወይ? ልክስ ነው ወይ የሚሉት ጥያቄዎች በንቃተ-ደናቁርት የህሊና አይን አና ጆሮ የሚገባ አይደለም።

አጨብጫቢነት (ኮንፎርሚስት ወደሚለው ትርጉም ሊጠጋ ይችላል) መልኩ የተለየ ከመሆኑ በስተቀር በበለጸገውም ዓለም አለ። ያሾማልም ያሸልማልም- በ”ኦፓርቹኒቲ” ስም። በተቃራኒ ንቃተ ህሊና አና ለህሊና መኖር ደሞ አንደ አብድ ሊያሳይ ይችላል። ባልበለጸጉ ሃግሮች አንደሚታየው ጡጫ አና አርግጫ በግላጭ ባይኖርም- ኣካልን ሳይነኩ ህሊናን ለመግረፍ የሚሞከር ሙከራ አለ። ይሄ አስተሳሰብ የኔ ብቻ አየመሰለኝ አልፎ አልፎ ደስ የማይል የ”ኦድ”ነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የካውንተር-ካልቸር” አንቅስቃሴ ጽሁፎችን ሳነብ ጉዳዮ ቀደም ብሎ ብዙ የተባለበት አንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ። በበለጸገው ዓለም ያለው አጨብጫነት አና እንደኛ ባለ ሃገር ያለው አጨብጫቢነት በህብረተስብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተመሳሳይ አይደለም። የበለጸገው ዓለም ምንም አይነት የፍትሃዊንት ጥያቄ ቢኖርም በልጽጓል። ይነስም ይብዛም ዜጎች ምርታማ ናቸው። እንደኛ ያንለውን ማህበረሰብ ግን የእድገት ሂደቱን መጎተት ብቻ ሳይሆን ባለበት ከመሄድም ሊያስቆመው ይችላል። በመለስ ዜናዊ ለቅሶ የታየው ምላሽ የሚያስደነግጠው ከዚህ አንጻር ሲታይ ነው። የህወሃት አጨብጫቢ ፓርቲዎች፣ አጨብጫቢ ፓርላማ ፣ አጨብጫቢ የፍትህ ተቋማት ፣ አጨብጫቢ ሚዲያ፣ አጨብጫቢ ሰራዊት ያነሰ ይመስል ፣ አጨብጫቢ ዜጋ በገፍ ማየት ከተጀመረ “በአንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሳይሆን መለስ ዜናዊን ገድሎኣል አንደሚባለው ነቀርሳ የከፋ ነገር ማስከተሉ አይቀርም። ለነገሩ የነበረብን ችግር አንደ አንቅርት ቀላል አልነበረም። ጫን ያለ ችግር የነበረ ቢሆን ነው አሁን የምናየውን ነገር አያየን ያለነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንደምክንያት መቀመጥ ያለበት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አሰራር ፣ቁርጠኝነት ማጣት አና ለፓለቲካ ትግል አንደግብዓዐት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ነገሮች በአጀንዳነት ይዞ ካለመስራትም የመነጨ ነው ባይ ነኝ። ባለፉት አርባ አመታት የተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎን ፋይዳ ለማሳጣት የተሄደበት ዋነኛ መንገድ ፍርሃትን መፍጠር ነበር። የፊውዳል ፓለቲካ ከመመኘት አንዳቆጠርብኝ አንጂ ቀደም ሲል በነበረው የፊውዳሉ የፖለቲካ ባህል ተቃዋሚም አንኳ ቢሆን ፈሪ አንዲሆን አይጠበቅም (አንዳንዴ የተቃዋሚውንም የመንግስትንም በሽኩቻ፣በግለኛነት አና በራስ ስልጣን ወዳድነት ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ አካሄድ ስናይ ያለፈው የተሻለ ነበር የሚያብልበት ሁኔታ ሊኖር ይቻላል) ። “በዛብህን [የሸዋውን]በዘውዴ አንጂ በወንድነት አልበልጠውም” ሲሉ አጼ ቴዎድሮስ የሚያስረግጡት ይሄኑኑ መሰለኝ። አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸው ድህነት ያልፈታቸው (የኮሶ ሻጭ ልጂ አልነበሩም አንዴ?!) እምነት ፣ግብረ ገብነት አና ያገር ፍቅር ማማ በውስጣቸው ሰርተው ከዚያም ዙፋን የደፉበትን ሂደት---ሙሉ በሙሉ በአጼ ቴዎድሮስ ተፈጥሮ ምክንያት ነው ለማለት ያስቸግራል። ያደጉበት ማህበረሰብ አና የመንግስት አስተዳደሩ ከፍርሃት በላይ ጀግንነትን የሚፈጥር በመሆኑ አና በህብረተሰቡም የነበረው ተቀባይነት ይመስለኛል። ዛሬ አንኳንስ መሳሪያ ካልያዘው ተቃዋሚ አና መሳሪያ ከያዙት አና ለህወሃት ከሚያጨበጭቡት እህት ድርጂቶች ቴድሮስ ወይ ገረሱ ዱኪ (ያገር ፍቅር) የሚንጸባረቅበት የፓርቲ አመራር የጠፋበት ምክንያቱ ምንድን ነው? መጥፋቱስ አንደፓለቲካ ችግር ታይቶኣል ወይ? በባህል ላይ የደረሰው ውርጂብኝ ውጤት ነው። በሃገራችን ውስጥ በመንግስት አካላት ቡራኬ ስትራይፕ ክለብ ሲፈጠር፤ ዜጎች ከዕለት ተዕለት ኑሮአቸው አና ከወደፊት አጣ ፋንታቸው ጋር ተያያዢነት የሌለው ጉዳይ (የአውሮፓን ክለቦች ሻምፒዮና ማስታወስ ይቻላል) በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሃገር ተረካቢ ነው የሚባለውን አምራች ዜጋ ቀልብ ሲገዛ ፤ ሃገር የመረከቡ ስራ ጭራሽ ሲረሳ ጉዳዮ በሃገር ህልውና አና መጻኢ ዕድል ያለውን ኣሉታዊ(አፍራሽ) ተጽዕኖ ተረድቶ ነገሩን ከቁም ነገር ጽፎ የተቃዋሚዎ ፓለቲካ ሁነኛ አጀንዳ ለማድረግ የተሞከረበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። ዛሬ ወጣቱን ህወሃት አንደ ባንክ ዘርፎት ለህወሃት ለቅሶም ሆነ ለህወሃት በዓል አደባባይ የሚያወጣበት ተጨማሪ ምክንያት ይሄው ነው። ህወሃት የደርግን ፈለግ ተከትሎ ጀግና በሚፈጠው ባህላችን ላይ ያደረሰው ጥቃት ይሄ ነው የሚባል አይደለም። ደርግም፣ህወሃትም፣ በሌላም ጎራ ተሰልፈው የነበሩ፣ ያ ትውልድ ፣ ተራራን እስክስታ ያስመታ አና ያዘለለለ ምናምን የሚባልለት ትውልድ የየፖለቲካ አጀንዳቸውን ከነበራቸው የባህር ማዶ ንባብ የቀዱት ቢሆንም የመታገያ ወኔ አና የመንፈስ ስንቅ ያገኙት ከባህላችን ነበር። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሁሉም በባህል ላይ ዘምተው የሚያታግለውን የመንፈስ ስንቅ ዝርፈው አልቃሽ አና ዘፍኝ ትውልድ ፈጠሩ። ባህልን በመዝረፍ ረገድ የህወሃት ወንጀል ግን ጠንከር ይላል።

ትንሽ ወጣ የሚል ርዕስ ቢመስልም ከዚሁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ አንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በከተማ የማይኖረው ህዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለው ግምት ውስጥ መግባት ኣለበት። እዛም አዘነተኛ በገፍ አንዳለ ስለሚነገርም ጭምር። ከ85 ፐርሰንት በላይ ሕዝብ በገጠር ይኖራል በሚባልበት ሃገር የተቃዋሚ ፓርቲዎች በገጠር የሚኖረውን ህዝብ ለመቀስቀስ የሚጠቀሙበት ዘዴ የገበሬውን የግንዛቤ ደረጃ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበረ? ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስለዜግነት መብቶች አንደወረደ በ”ሊበራሉ” ዘየ አያወሩ ነው የሚቀርቡት (ይቀርቡታል ወይ የሚለው ጥያቄ ሆኖ ነው አንግዲህ)? ወይንስ አንደሚገባው ከባህሉ፣ከወጉ አና ከግንዛቤ ደረጃው ጋር አንዲሄድ አድርገው ያቀርቡለታል የሚለው ጥያቄ ነው። በገጠር ያለው ማህበረሰባችን አምላኩን የሚፈራ አና ግፍን የማይወድ አንደሆነ አንድና ሁለት የለውም። ስለምን የህወሃት የግፍ ፓሊሲ ተባባሪ( በእህት ድርጂቶችም በኩል ቢሆን) አና መሳሪያ ሊሆን ቻለ? በዚህ መንግስት ፓሊሲ የተረገጠ ሆኖ ሳለ ስለምን የህወሃት አዘነተኛ ሆነ? ሰሞኑን አንድ ሰው ያጫወተኝን ላካፍል። የተወለደበት ጎጃም ደንበጫ ሚባል ቦታ ለአረፍት ሄዶ ያጋጠመውን ነው ያወራኝ። ከዘጠና ሰባት ምርጫ ጋር ተያይዞ የተገለለ አና ክትትልም ጭምር የሚደረግበት ዘመድ አንዳለው ነገረኝ። አናም ከጓደኖቹ ጋር ሻይ ሊጠጣ ይጠራቸው አና ጓደኞቹ አንዲገለል የተወሰነበት ክትትልም የሚደረግበት ሰው ጋር መሆኑን ሲያዮ ፈሩ። ፍርሃታቸውንም ሳይደብቁ አስረድተውት ለመሄድ አንደማይፈልጉ ነገሩት። ምን ይሄ ብቻ ክትትል አንዲደረግበት የተወሰነበት ሰው ተወልዶ ያደገበትን ከተማ ከረዢም ጊዜ በኋላ የሄደ ዘመዱ ጋር በመታየቱ ጸጉረ ልውጥ ሰው ጋር ታየ ተበሎ ለከተማው ደህንነት ሃላፊ ሌሊት በስልክ ተነግሮት ኖሮ ከአንቅልፉ ባንኖ ተነስቶ “ጸጉረ ልውጡን” አደን ጀምሮአል። ሲያገኘው አና ልጁን ሲያናግረው የሆነው ነገር ሌላ ነው። ያገሩ ልጂ በትምህርት ምክንያት ርቆ ሄዶ የኖረ አና ዘመዶቹን ለመጠየቅ የመጣ አንደሆነ ተረዳ። በሌላኛው የጎጃም ክፍል ተመሳሳይ ነገር የለም ማለት ይከብዳል ከሁኔታው። የሃሳብ ልዮነት ያለው ዜጋ ለምን የደህንነት ክትትል ይፈረድበታል የሚለው ጥያቄ አንደተጠበቀ ሆኖ ፤ ጎጃም ለማያውቀው ህወሃት ስልጣን ሲል የራሱን ወገን አስከመሰለል አና ምናልባትም አሳልፎ አስከመስጠት የሚደርስ ሰው አንዴት ሊገኝ ቻለ? አንዴት ጎጃም ወየነ? ንቃተ-ደናቁርትነት አንዴት ነገሰ የሚለው ትያቄ መልስ ብቻ ሳይሆን መፍትሄም የሚያስፈልገው ነው።

የገጠሩ ህዝብ ብዙ ጊዜ “ሳይማር ያስተማረን” አየተባለ ቢገለጽም ሳይማር የተማረም ነበር! ነውር ያውቃል። የተዛባ ፍርድ መለየት ይችላል። የግፍ ተባባሪ አይሆንም። በራሱ መንገድ ንቃተ-ህሊና የነበረው ነው። ያንን ንቃቱን ላለፉት አርባ አመታት ሲዘረፍ የኖረ ቢሆንም አሁን የተነሳው ተቃዋሚ አንደኛው ስራ መሆን የነበረበት ሁኔታውን በጥሞና ተረድቶ ስነ-ልቦናውን ግምት ውስጥ አስገብቶ አየተነጠቀ ያለውን ንቃተ-ህሊናውን አያስጠበቀ የለውጥ ሃይል አና ባለቤት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ስራው ቀላል ነው። ያለምንም ችግር መስራት ይቻላል ከሚል አምነት አይደለም። ግን አንዲህ አንዲህ ያለው ስራ ካተሰራ አና በገጠር ያለው ትኩስ ሃይል በባለቤትነት ስሜት የሃገሩ ፓለቲካ አካል አንዲሆን የሚመላከትበት ሂደት ካልጠፈጠረ ህወሃት ፀጉረ ልውጥ ባልሆኑ ሰዎች አማካይነት ንቃተ-ደናቁርትነትን አያስፋፋ ሲያስፈልገው የሚያስጨፍረው ሲያስፈልገአው የሚያስለቅሰው የፓለቲካ መሳሪያ አድርጎት ይኖራል። በዚህ ሂደት ሀገር ህወሃት በሚያዘጋጃቸው የራሱ ተተኪዎች አየወደቀች ሌላው “አስተዋይ አድናቂ” ህወሃት ደሞ አስተዋይ መሪ ፈጣሪ አየሆነ ሃገር በህወሃት ቅብብሎሽ ልትወድቅ ትችላለች።

በሶስተኛ ደረጃ ምክንያት ነው ብየ ያሰብኩት ነገር በከተማ የነበሩ ንቃተ-ህሊና የማነጽ አና ግንዛቤ የማስፋት አቅም የነበራቸው ዜጎች ህወሃትም ዘመኑም ብፈጠረው “የኑሮ ግብ”-ስደት-ሰለባ መሆን ነው። በዓለማችን ታሪክ ውስጥ ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ከውጭ ሆነው የለውጥ እቅድ በመንደፍ አብዮት አና የፖለቲካ ለውጥ የፈጠሩበት ሁኔታ አንዳለ ማስታወስ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሆ ቺ ሚኒ( ሶሻሊስትነቱ ለጊዜው ይረሳ---የተነሳበት አገባብ ሌላ ስለሆነ) በእንግሊዝ አና በፈረንሳይ በስደት የኖረ አና በምግብ አብሳይነት ኑሮውን ይገፋ የነበረ ሰው ነው። ሲያምን ግን አመነ። ግንዛቤውን አዳብሮ ታግሎ ያታገለ መሪ ነበር። ሊዮን ትሮትስኪ (ሌኒንም ራሱ) የታላቁን የጥቅምት አብዮት ጥንስስ የሰሩት በቪየና የካፌ ቼንትራሌን ቡና አያወራረዱ ነው። በነገራችን ላይ ትሮትስኪ ለፖለቲካ ስራ ወደ ሃገሩ ሲገባ አንኳን ሞርጌጂ ያልከፈለው የቡና ዕዳ ነበረበት። እጂ አና አግሩን ይዞ ነው የተመለሰው። አንደ ቸ ጉቬራ ደሞ ከሃገር ሃገር አየሄዱ ለተጨቆነ ህዝብ ሁሉ የመታገል ህልም የነበረው አና የሞከረውም ነበረ። በተቃራኒው የአኛ ሃገር ስደተኛ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን ለውጥ ጥሩ ሞተር ሊሆን ይችል የነበረ አና በተወሰነ መልኩም የነቃው ነው የተሰደደው። ምን ሰራን? የስታርባክሱ ፖለቲካ የፈጠረውም ሆነ ሊፈጥር ያሰበው እዚህ ግባ የሚባል የለውጥ እቅድ ያለ አይመስልም። አልፎ አልፎ በፓለቲካ ወሬ መሃል የሞርጌጂ ወሬ ሁሉ የሚያወራ አይጠፋም። በየተሰደደበት ሃገር ተመሳስሎ ለመኖር አውቆትም ሳያውቀውም ራሱን ቀየረ። በራሱ የመጣውም ማህበራዊ አስተሳሰብ ለውጥ (አጨብጫቢነትን ጨምሮ) ወደ ሃገር ቤት የላከም አይጠፋም። ባንድ ጎኑ ሳየው በሃገራችን በደረሰው የማህበራዊ አስተሳሰብ ክስረት ይነስም ይብዛ የወጣነው ሰዎችም አጂ አንዳለበት ይሰማኛል። ዛሬ የኢትዮጵያ ወጣት በህወሃት ሲዘርፍ ተዘረፍክ የማለት የሞራል ብቃትስ አለን ወይ የሚለው ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው።

ከላይ አንደምክንያት የዳሰስኳቸው አንዳልኩት ፊት ለፊት የተከሰተልኝን ሃሳብ ለማካፈል ያህል አንጂ ችግሩ ይጠና ቢባል ተጨማሪ ወይንም ከዚህ የተለየ በርካታ ምክንያቶች ሊገኙ ይችላሉ። ወደ ማጠቃለያ ሃሳቤ ስመጣ -መለስ ሞተ። ደጋፊዎች አሉት። ቤተሰብ ወዳጂ ዘመድ አሉት። ሃዘናቸው ይገባኛል። ይገባቸውማል። ከዚያ ሲያልፍ ግን መለስ ዜናዊ ሲመራው በነበረው ስርዐት ሲረግጡ የነበሩ ዜጎች የደረሰባቸውን አና በወገኖቻቸውም ላይ ጭምር የደረሰውን ግድያ አና አፈና ዘንግቶ “ሰማይ የተደፋ” ይመስል እየየ ማለቱ የአስተሳሰብ ቀውስን አመላካች ይመስለኛል። ከባህላችን “ለሞተ ሰው ማዘን” ጋርም መያያዝ የለበትም። የአቶ መለስ ሞት ለህወሀት ፓለቲካ ነው። ስለሆነም ነው ለረዢም ጊዜ ማህበራዊነትን ረስቶ ጉዳዮን በሚስጥር በህወሃት ሰዎች ብቻ አንዲያዝ አድርጎ የነበረው። በውስጡ ያለውን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጨርሶ አደባባይ ሲያወጣ የአቶ መለስብ ሞት የህጋዊነት መገንቢያ ጡበ አና አርማታ ሊያደርገው ፈለገ። በባህል ስም እየየ ሲባል ህወሃት ጉዳዮን አንደ ባህል ሳይሆን የሚረዳው ( የነሱ ባህል ሌላ አንደሆነ አቶ በረከት ስሞን አንደነገረን እንዳይረሳ) የፖለቲካ ምንዛሬ አድርጎ ተቀባይነትን አንደማሳያ ተጠቅሞ የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የበለጠ አፈና ሊያደርስ ይችላል።

ጠሚው ከሞቱ በኋላ የተሰጣቸው ትክለ-ስብዕና (ኢሜጂ) መጋነን ብቻ ሳይሆን ፈር የለቀቀ አናበሃሰትም የተሞላ ነው። መጥፎ ጎን አንደነበራቸው ሁሉ ጥሩ ጎንም ነበራቸው አያሉ ለሚያወሩ አባባላቸው ትክክል የማይሆንበት ሁኔታ አለ። መጀመሪያ ነገር በዚህ በሰለጠነ ዘመን ሃያ አንድ አመት ሙሉ በጉልበት በላያችላን ላይ የኖረን ሰው አንደባለውለታ ማየቱ ካላዋቂነት ሌላ ምንም ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ሁለተኛ ነገር መለስ ዜናዊ የሰራው ስህተት በስራ ሂደት አንደሚፈጠር ስህተት አድርጎ ማየቱ ፈጽሞ ስህተት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ህይወት በገፍ የጠፋው፣ ዜጎች በጂምላ ወደ አስር የተወረወሩት፣ አሰቃቂ ድብደባ የደረሰባቸው አንድ ጊዜ አይደለም። ሁሉት ጊዜ አይደለም። የዜጎች ህይወትን ከማጥፋት ጋር የተያያዘ ድርጊት አንደወንጀል አንጂ አንደ ስህተት መታየትም የለበትም። ተጠያቂነት አና የህግ የበላይነት የኖረበት ሃገር ቢኖረን ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አኳንስ ሃያ አንድ ዓመት በስልጣን ሊቆዮ በመጀመሪያው የአምስት አመት የስልጣን ዘመናቸው በፈጸሙት ወይንም ባስፈጸሙት ወንጀል ፍርድ ቤት መቆም የሚገባቸው ነበሩ። ይሁን ያ ሁሉ ቀረ። የአምላክ ፍርድ አና ፈቃድ ቀደመ። አንዲህ ሲሆን ያደረጉትን ነገር ይቅር አንበላቸው ቢባል አንኳ፤ ህወሃት ሃዘኑን ተጠቅሞ፤ የለቅሶ እቅድ አና በጀትም ጭምር አውጥቶ( የተከፈላቸው ሰዎች አንዳሉ ተሰምቶል--የትራንስፓርት አቅርቦቱ አና ሌላ ሌላውም ) የሌለ የጻድቅ ገጽታ ሲያላብሳቸው እሱን ተቀብሎ ማራገብ አያስፈልግም። ሰው መሆናቸውን የሚያጠራጥር ገጽታ ነው የተገነባላቸው። መለስ ዜናዊ ለሃያ አንድ አመት በስራው ላይ አንደመቆየቱ ለህወሃት “በሚጠም” መልኩ ስራውን ኣቀላጥፎ የመስራት ልምድ ሊያካብት አንደሚችል ጥያቄ የለውም። ያ ማለት ግን የተለዮ ሰው ናቸው አያስባለ ሊያደናቁር የሚገባው ነገር አይደለም። ስብሃት ነጋ ከቁም ብዙ ጊዜ የሚናገሩትን ከቁም ነገር ቆጥሬ የማላውቅ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡት አስተያየት ግን ሚዛናዊ ነው አላለሁ። ፋጢማ ፣ከበደ ፣ እገሌ ---ያው ናቸው። ይሄን ያህል ልዮነት ሊኖራቸው አይችልም። ለመሆኑ በኦህዴድ፣ በብአዴን አና በደህዴን ያሉ “ለትራንስፎርሜሽኑ አቅድ” ከጠሚው ጎን ተሰልፍው የሰሩ (“ልማት” በሚባለው ነገር ውስጥ የደከሙም ይኖራሉ። ምናልባት ከተቅላይ ሚኒስትሩ አኩል) ይሄ በህወሃት ለመፍጠር አየተሞከረ ያለው የፖለቲካ ገጽታ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለው ችግር ታይቶአቸዋል? ለመሆኑ በትውልድ እየተቀለደ እስከመቼ ነው የሚኖረው?? የህወሃት አህት ድርጂቶች የወንጀል ተባባሪ በመሆን በንቃተ-ደናቁርትነት መንፈስ የሚቀጥሉትስ አስከመቼ ነው?

Blog Archive