(በቅድሚያ የአማርኛ ስርዐተ-ነጥቦችን ባግባቡ ጠብቄ ስላልጻፍኩ በትዕግስት እንድታነቡኝ እጠይቃለሁ:: የተፈጠሩ የአማርኛ ግድፈቶችም ካሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ::) መልካም ንባብ!
በዚህ ዘመን አሉ ከሚባሉት የሙዚቃ ሰዎች ውስጥ ቴድሮስ ካሳሁንን በግንባር ቀደምነት የማስቀምጠው ቴድሮስ ባለው የድምጽ ቅላጼ እና በሚደርሳቸው የሚመስጡ ዜማዎች ብቻ አይደለም:: ግጥሙን ራሱ ስለሚጽፈውም ብቻ አይደለም:: ከዚህ ባለፈ በግጥሙ ውስጥ የሚንጸባረቁ መልዕክቶች እና ያላቸው ሀገራዊ ፋይዳ ነው ቴድሮስን ለየት የሚያደርጉት:: ያደገበትን ማህበረሰብ ወግ ባህል እና እምነት ከማንጸባረቅም በተጨማሪ ዘመን የወለዳቸውን የህዝብ ስነ-ልቦና መመሰቃቀል እና ችግር ተረድቶ በሙያው ችግሩን በመቅረፍ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጾ ቴድሮስን ከድምጻዊነትም ያስበልጠዋል:: የጥበብ ሰውን ሀገራዊ ፋይዳ የምንሰፍረው በዚሁ ይመስለኛል::
ህሊናውን ያለምንም ስጋት እና ጸጸት የሚሸጥ እየበዛ መምጣቱን ያስተዋለው ቴድሮስ (የማይሸጡ እና ለእምነት የሚሞቱ እንዳሉ አውቃለሁ!) "ዋሽቶ ከመኖር ...አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር'’ በሚለው ዘፈኑ ያደግንበትን ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ስለህሊና ክቡርነት አስታውሶናል:: መንፈሳዊ ህግን እና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብን አስተሳስሮ የያዘ የሰው ልጂን ለእውነት እና ለፍትህ የሚያተጋ ማህበረሰባዊ ተልዕኮ ; ፋይዳ ብሄራዊ እና መንፈሳዊ ግዴታንም ነው ያስታወሰን:: ጽድቅስ ቢሆን የሚመጣው ከእምነት በተጨማሪ ከህሊና ንጽህና አይደለም እንዴ??በየትኛውም ዘመን እና ቦታ ለሚኖር ትውልድ እውነትም ከህሊና ንጹህነት በላይ ሰውን የከበረ የሚያደርግ ነገር ስለሌለ የሰው ልጂ ህሊናውን በጥቅም ሲቀይር የሚዘፈቅበትን የንዳማ አሮንቃ የሚያስታውስ ዘፈን ነው::
ከዜማ ዘመን ተሻጋሪነት ጋር በተያያዘ በዘመናችን ስለምናውቀው እና ስለምንመሰክርለት ቴድሮስ እንደመግቢያ አነሳሁ እንጂ አነሳሴ ስለ ቴዲ አፍሮ ለመጻፍ አልነበረም:: እንደሀገራችን አቆጣጠር በሰባዎቹ ውስጥ ከተቀነቀኑት ዘመን ይሻገራሉ ስለሚባሉ ( ዘመን የማይሽራቸው ) የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ ---በነሙሉቀን መለሰ ; ማህሙድ አህመድ; ኩኩ ሰብስቤ እና ጥላሁን ገሰሰ ድንቅ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ የሌላ ሰው እንጂ እንዳለበት ሰሞኑን ባየሁት አንድ ኢንተርቪው ስለተረዳሁ እጂግ በጣም ስለገረመኝ ነው::
የዓለምፀሀይ ወዳጆን ታዋቂ ተዋናይነት እየሰማሁ ባድግም ከዚያ ባሻገር ድንቅ ገጣሚ እና ጸሀፊ ስለመሆኗ የማውቀው ነገር አልነበረም:: በአሜሪካ ራዲዮ የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም በተለያየ ጊዜ እየቀረበች በተለያዮ ጉዳዮች ላይ ቃለ መጠየቅ እንደሚደረግላት አስተውያለሁ:: በቅርቡ ደሞ ስለ እናት እጂግ ግሩም የሆነ ግጥም አእንዳቀረበች አውቃለሁ:: ከዚያ ውጭ ዓለምፀሀይ ድንቅ ገጣሚ እና ጸሀፍት ስለመሆኗ ያወቅኩት ከዚህ ቃለ-መጠየቅ ነው::
ከታች ባለው የዓለምፀሀይ ቃለ-ምልልስ የምናውቀው ስለእሷ ብቻ አይደለም:: ካስተዋልን ሌሎች ብዙ ነገሮችን ማየት እንችላለን:: በዘመኑ የነበረውን ማህበራዊ ሁኔታ ; የወጣቱን ስነ ልቦና ; የነበረውን የፖለቲካ ተሳትፎ; በመምህራን እና ተማሪዎች መካከል የነበረው ግንኙነት; በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ እንኳን የነበረው ማህበረሰባዊ ሀላፊነትን የመወጣት ስሜት እና ትጋት; ወጣቶችን በመቅረጽ ረገድ የነበራቸው ተሳትፎ እና የትወና ጥበብ በሀገራችን መሰረት እና ፋይዳ እንዲኖረው ደፋ ቀና ስላሉ እና በውል ስላልተዝከሩ ሰዎች ትናገራለች::
በተለይ ትኩረቴን የሳበው ህይወታቸውን ለሀገር መስዋዕትነት በመክፈል እና በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በአምባ ህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል አስባስቦ በእንክብካቤ እና ፍፁም ኢትዮጵያዊ በሆነ ሁኔታ ቤተሰባዊ ፍቅር እየሰጡ ለማሳደግ የተደረገው ጥረት በእውነት ልብ ይነካል:: ጨካኝ በሚባለው በደርግ ዘመን እንኳን ይህን ማድረግ ተችሏል! እንዲህ ያለው ነገር ያለውን ማህበራዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ለመረዳት አሁን በህወሀት (TPLF) መንግስት የህግ እና የፖለቲካ ከለላ ሴት እህቶቻችን በገፍ ( ሰሞኑን ባለኝ ንባብ በወር እስከ 45, 000 ድረስ) በባርነት መልክ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚላኩበትን ሁኔታ እና ህወሀት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን በማደጎ እያወጡ ለባዕዳን በመስጠት ረገድ ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛው መንግስት እንደሆነ ከተረዳሁ እና የኢትዮጵያ ህጻናት ለማደጎ እየቀረቡ ለህወሀት እና ለስርዐቱ ደጋፊዎች የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆኑበትን ሁኔታ ስናስብ ያኔ ለተሰራው ስራ ዋጋ እንድንሰጥ ያደርገናል:: ዓለምፀሀይ በህጻናት አምባ ህጻናት ህይወት የነበራትንም ተጽዕኖ ለማወቅ ችያለሁ:: ኮሌጂ እያለሁ ከህጻናት አምባ የመጣ አንድ ጓደኛ ነበረኝ በጣም አስቂኝ እና የቲያትር ዝንባሌም የነበረው ነው:: ምክንያቱ የገባኝ ግን አሁን ነው::
ከዚያ ውጪ ወደ ዓለምፀሀይ ሁለገብ ሰውነት ስመለስ የፖለቲካ ተሳትፎ አንዱ ገጽታ ነበር:: እንደገባኝ ድሮ ፖለቲካ ህወሀት እንደሚያደርገው መጀመሪያ ትውልድን አደገኛ ቦዘኔ ብሎ በሽብር አንቀጥቅጦ ሲያበቃ መለስ ብሎ ደሞ የእኛ ደጋፊ ከሆንክ የደህንነት ዋስትና እና እንዳቅምህም መንደላቀቂያ ታገኛለህ ተብለው ስለተስፈራሩ የሚገቡበት አልነበረም:: ፖለቲካ የእምነት ነገር ነበር:: ደርግን የወደደ ከደርግ ኢሀፓን የወደደ ( በህቡዕም ቢሆን) እንደየእምነቱ የሚገባበት ነበር:: የደህንነት ዋስትና ለማግኘት ደርግ ጋር የገቡ አይኖሩም ለማለት አይቻል ይሆናል:: ያኔ የነበረው ስርዐት የለየለት የቅጥረኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ እያወቁ ይገቡ ነበር ለማለት ግን ያስቸግራል:: ፖለቲካ የፍርፋሪ መሰብሰቢያ አልነበረም:: (በነገራችን ላይ ስለ ህወሀት ጨካኝነት እና ሀገር አጥፊነት ስናስብ ልንዘነጋው የማይገባ ጉዳይ የሰው ልጂን በዚህ ዘመን ልክ እንደባሪያ የፖለቲካ ባሪያ አድርጎ በፍርፋሪ መግዛት ራሱን የቻለ - እንደውም ለመጭውም ትውልድ ጭርም የሚተርፍ ቶርቸር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል:: ማዕከላዊ እያስገቡ የሰውን አካል የሚገርፉት ነገር ወንጀል ቢሆንም አካል ያገግማል:: ጉልበት አለኝ ብሎ ዘጎች በገዛ በሀገራቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ ካስራቡ በኍላ ህሊናቸውን በፍርፋሪ መግዛት ከአካል ግርፋት የበለጠ ኢ-ሰብአዊነት እንደሆነ የተዘነጋ ይመስለኛል::)
ከፖለቲካው ተሳትፎ ውጪ ደሞ ዓለምፀሀይ ከላይ ለጠቃወስኳቸው ሀገራችን ባፈራቻቸው ድንቅ ድምጻውያስ ስራ ውስጥ አሻራዋን ትታለች:: ሙሉቀን መለሰን ስናስን ""ቁመትሽ ሎጋ ነው"" ""እንደኔው አእምሮ"" ""መውደዴን ወደድኩት"" ልንረሳ አንችልም:: እነዚህ ግጥሞች የዓለምፀሀይ ወዳጆ እንደነበሩ ያወኩት ከዚህ ኢንተርቪው በኍላ ነው:: የጥላሁን ገሰሰን ""ኢትዮጵያ"" የሚለው ዘመን የማይሽረው ዜማ (ህወሀት ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት እስካልተሳካለት ድረስ ማለቴ ነው) ግጥም የዓለምፀሀይ ወዳጆ ነው:: የኩኩ ማራኪ ""ደኔ በለው"" ዜማ ግጥም የዓለምፀሀይ ወዳጆ ነው:: ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ዜማዎች አሉ::
በኢንተርቪው ላይ ዓለምፀሀይ የጥበብ ሰው ዋጋ በገንዘብ እንደማይተመን የተናገረችው ነገር ልብ ሊባል ይገባዋል:: የጥበብ ሰው ዋጋው የህዝብ ፍቅር ነው:: ከሊስትሮ ጀምሮ እስክ እውቁ የህክምና ሰው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ! ለዓለምፀሀይ የተንጸባረቀው ፍቅር ዓለምጸሀይ በተሰጦዋ በሙያ አንጻር እና በሌላም መልኩ ለሀገሯ ቁም ነገር ያለው ስራ ስለ ስራች ይመስለኛል:: ዓለምፀሀይ ለምን እንዲህ ሆነች ነው ጥያቄው?? ዓለምፀሀይ ተሰጦዋ በተፈጥሮ ያገኘችው ቢሆንም ተሰጥኦዋን ተረድተው ያበረታቷት እና ወደ ውጪ ያወጡላት መምህራኖቿ እንደሆኑ ተናግራለች:: በተሰጦዋ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ስራ እንድትሰራ ተልዕኮ የሰጣት ሀላፊነት የጫነባት ግን አስተዳደጓ የኢትዮጵያዊነትን ፋይዳ እና ለኢትዮጵያዊነት የተከፈለውን መስዋዕትነት በማወቋ የኢትዮጵያውያን ባህል እና እምነት ለኢትዮጵያውያኖች ያለውን ፋይዳ እና ትርጉም በየዕለቱ እየኖረችው ስላደገች ነው:: ተሰጦውን ለንግድ ተግባር እና ለሀብት ማካበቻነት መጠቀም እና ተሰጦን ለሀገር እና ለህዝብ መታመኛነት ማዋል ከፍተኛ ልዮነት አላቸው:: ልዮነቱን ማወቅ እና የበለጠ የህይወት ርካታ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ የክብር ልብስ የሚያጎናጽፈውን ለይቶ ለማወቅ በትክክል ማሰብ እና የህይወትን ትርጉም መረዳት ይጠይቃል:: ይሄ ደሞ ከእውቀትም የሚመጣ ነው::
ባካበቱት ሀብት ከሚታወቁ ሰዎች ይልቅ በተሰጥኧቸው የህዝብን ክብር እና ሞገስ ያተረፉ የበለጠ ዘላለማዊ ናቸው:: ብዙ ጊዜ ""ህይወት አጪር"" ናት የሚል አባባል እሰማና ከዚህ በኍላ የሚከተለው ዓረፍተ ነገር ""ተደሰት ጨፍር"" አይነት ነገር ይቀናዋል:: በዚህ አስተሳሰብ ምክንያት አንዳንዶች ሳይራቡም ህሊናም መሸጥ ጣጣ ውስጥ የሚገቡት ከዚህ ትርጉም አልባ ከሆነ አስተሳሰብ በመነጨም ነው:: ህይወት አጭር ከሆነች ከመጨፈር እና ጭፈራ ባቆመ ማግስት በሚጠፋ ደስታ ያለፈ ፋይዳ ሊኖራት ይገባል:: ህይወት አጭር ከሆነች ለእምነት እና ለእውነት ልንኖርባት ይገባል:: ህይወት አጭር ከሆነች ከትውልድ ትውልድ በዘመን ውስጥ በጥሩ መንፈስ ሊተላለፍ የሚችል ቁምነገር የሚሰራባት መሆን አለባት::
ዛሬ ብዙዎቹ አርቲስቶች ንቃተ ህሊናቸው በደንብ ያልዳበረ ንባብ እና እውቀት የሌላቸው ከመሆናቸው የተነሳ የህወሀት መንግስት እየሰራ ያለውን የማስመሰያ ስራዎች በአግባቡ ባለመረዳት ; የህወሀትን አጭበርባሪ ባህሪ እና ጸረ-ኢትዮጵያ ባህሪ ጠንቅቆ ባለማወቅ የተነሳ የስርዐቱ ደቀ መዛሙርት በመሆን ራሳቸውም ደንቁረው ህዝብም ሊያደነቁሩ እየሞከሩ ነው:: እንዳይማል አልፎ አልፎ አንዳንድ አርቲስቶች አሉ:: እኔ እንደገባን እንደሜሮን ጌትነት ያሉት አርቲስቶች እንደ ዓለምፀሀይ የመሆን እድል ያላቸው ይመስላል:: ሌሎችም አንዳንድ አይጠፉም:: እንደነሰራዊት ፍቅሬ ያለ የስዳይ ዱባም አለ!
ከዓለምፀሀይ ጋር የተደረገው ቃለ-መጠየቅ በተለይ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሊያዮት የሚገባ ነው እላለሁ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!