Sunday, April 15, 2012

"ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን "?

ምንም እንኳን በአካል ሀገራችን ባንሆንም በመንፈስ እዛው ነን:: በተለይ እንዲህ ባለ የአውደ ዓመት ጊዜ:: በመገናኛ ዘዴው መርቀቅ እና ፍጥነት ምክንያት የመረጃ ልውውጡ የዛኑ ያህል ስላደገ እና የየደቂቃውን ጭምር መረጃ ማግኘት ስለሚቻል አሁን አሁን ሀገራችን ያለነው በመንፈስ ብቻ አይደለም ለማለት ያስደፍራል:: እዛው ያለሁ ያህል የማውቃቸው ጉዳዮች አሉ:: በዓይኔ በብረቱ ካላየሁ የሚባል ነገር ብዙም ትርጉም አይሰጥም በዚህ ዘመን:: እንዳይኔ ወይንም ከዚያ በላይ ሆነው ነገሮችን በሚዛናዊነት በመመዘን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚያቀብሉ ወገኖች ሳላሉን::

ትንሳኤ እንደመሆኑ እንደደንቡ ቤት ውስጥ እንዲኖር የሚያስፈልገውን የአውደ ዓመት መሰናዶ አድርጌ በላሁ ጠጣሁ ( እየጠጣሁም ነው በስሱ):: እየተሰማኝ ያለው መሳቀቅ (ብቸኝነቱን ለምጀዋለሁ) ግን እንዲህ እንዳይመስላችሁ:: ብዙ ወገኖቻችን በምን አይነት ሁኔታ እንደሚያሳልፉት እያስታወስኩ ነው:: የዶሮ እና የበግ ዋጋ ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ የሚተው ነገር ሳይሆን የኢኮኖሚ የባህል እና ማህበራዊ አንደምታው መመርመር ያለበት ነገር ነው::

ከቁም ነገር አዘል ቀልድ ጀምሮ እስከ ጠንከር ያሉ ዘገባዎች እና አስተያየቶች ተሰንዝረዋል:: ""እንደ እየሩሳሌም እንዳክሱም ጺዎን ተሳልሜው መጣሁ ዶሮና በጉን"" የሚል መልዕክት አንብቤ ከቀልድነቱ ይልቅ ሮሮነቱ ስላየለብኝ ምን መዐት መቶ ነው ዋጋ እንደዚህ ሰማይ የነካው ከሚል ሀሳብ ጋር ብዙ ቆየሁ:: በኔ እንኳን እድሜ ዶ/ሮ ከ5-10 ብር ባለው ሬንጂ ሲሸጥ አስታውሳለሁ:: ትልቅ የሚባል በግ በ75 እና 80 ሲገዛ አስታውሳለሁ:: እውነት ነው የብሩ የመግዛት አቅም እንደተዳከመ ይታወቃል:: በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ግን ከመቶ ፐርሰትን በላይ የብር የመግዛት አቅም ሲወድቅ ምን እንደሚባል አላውቅም:: የሚገርመውን የአብዛኛው ሰው ገቢ ትርጉም ባለው ሁኔታ አለመጨመሩ ነው::

እየሆነ ያለው ነገር በቅንጂት እየተሰራ ያለ ነገር እንደሆነ መገመት ይቻላል:: የማን የማን እጂ እንዳለበትም መገመት ይቻላል:: በበዓል ቀን በግና ዶሮ ገዝቶ ከዘመድ ወዳጂ ጋር መቋደስ ለእርድ እና ለስጋ ያለን ፍቅር ሳይሆን የሚያመለክተው ማህበራዊ ፋይዳውን እና ባህላዊ ፋይዳውን ነው:: ብዙ ኢትዮጵያውያን እጂግ በጣም ደሀ እየሆኑ በሄዱበት ሁኔታ ትርጉም እና ክብር በሚሰጣቸው በዐል የሚገለገሉበት ሸቀጥ ላይ ቅጥ ባጣ ሁኔታ ዋጋ መቆለል በአነስተኛ ገቢ ባላቸው ወገኖቻችን ላይ ሳይሆን በባላችንና በማህበራዊ ግንኙነታችንም ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት መቆጠር አለበት:: ጥቃቱ የሚሰነዘርብን ለመጠቃት የተመቸን ስለሆንን እና ለለውጥ ስላልተነሳሳን ነው:: እንደ ህዝብ ስለማንፈራ እና ምን ያመጣሉ ስለምንባል ነው:: እንዲህ ባለ ሁኔታ መፍትሄው ዶ/ር ኃይሉ አርዐያ በመጨረሻው የፍኖተ ነጻነት እትም በሰጡት አስተያየት እንደሚሉት ""ያስጠቃን ባህላችን ነው:: የባህል ባሪያ ስለሆንን ነው:: ዶ/ሮ በ200 ብር ገዝቼ አላድርም ባህሌ ይቅር"" ሳይሆን የተቀናጀ በማይመስል ምናልባት ግን በደንብ በተጠና እና በተቀናጀ ሁኔታ በባህላችን ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ያሉ ሀይሎችን ለይቶ መታግል ያስፈልጋል::

No comments:

Post a Comment

Blog Archive