Monday, April 6, 2009

የረሐብ አድማ !


ቆሽቱ ሲጨስ እርር ሲል
አሳራሪውን ያሳርር ይመስል
ተሜ እንደውም አልበላም ቢል
አሳራሪዎቹ ስለገባቸው
አልበላሙ እንደማይጎዳቸው
ለምደውት ፈለጉና ሊላጡበት
ይሉ ጀመር ተውት አትለምኑት ::

እውነትም ምን አስራበው ?
ምሳ እያለው ቁርስ እያለው
ቅንጨው ዳቦው ሞልቶ በየካፌው
እራቱንም ሳያጣው !
ተሜ ያንማ መች ሳተው ?!

እርር ያለው የተራበው
ባገሩ ላይ በሚሆነው
ወገኑን ሲያየው ሰልስሎ
ያለ ዕድሜው ተጎሳቁሎ
ቀንበር ጠቦት ተመሳኩኖ
ማደሪያ መሬቱ ተሸንሽኖ
እንደሚራብ ስለገባው
ተሜ የካፌውን እንዴት ይብላው ?!

የገበሬው እኗኗሩ
መኳተኑ በባዶ እግሩ
እንደማያርስ ጦም ማደሩ
ያም ሳያንሰው ዱላና እስሩ
ሰቆቃው ስለገባው
ተሜ የካፌውን እንዴት ይብላው ?!

መናገር ዳዳው
ግና ዱላ እስሩ አፈናው ትዝ አለው
ዙሪያውን ሲማትር
ባለክላሽንኮቭ አጋዚ ወታደር
አብሮት ያለው ወሬ ሰላይ የታጠቀ
በግቢው ውስጥ የሸመቀ
ዝም እንዳይል
ለህሊናውስ ምን ይበል ?!

ያን ሲያነሳ ይኼን ሲጥል
ሲብሰከሰክ ሲያሰላስል
የካፌው ወጡ ቀጥኗል
ላይብራሪው መጽሐፍ አንሶታል
መች ተወው መብሰልሰል
የግንባሩን ጸጉር ሲፈትል ሲፈትል
ሲያስታውስ ለካስ አለ የራብ አድማ
ባጋዚ ቆመጥ የማያስደማ ::

እሱም ቢሆን በሰበብ ነው
የወገንን ጉዳይ ማን ሊደፍረው
ባሳራሪው ቋንቋ ያ ፖለቲካ ነው
እሱ ደሞ ወንጀል ነው ላሳራሪው
ማንስ ሊያስወራው
ምን ሊሰራ ጆሮ ጠቢው
የታጠቀ በጊቢው ውስጥ የሸመቀው
የተሻላው የራብ አድማ
በቆመጥ የማያስደማ ::

እስቲ በየት ሀገር
ታይቷል ራብ ሲያስጨፍር
አድማው ሲጀመር
ልክ መራብ እንደሚያጠነክር
ይጀመራል ፉጨት
ግንብ አጥር ላይ መወራጨት ::

ቀረርቶው ሌልኛ በእንግሊዝኛ
ባማርኛ በኦሮምኛ በትግሪኛ
""ጥያቄያችን የዳቦ ነው !""
ዳቦ ሞልቶ በየካፌው

የኮሌጁ አስተዳዳሪ
ባለ ጊዜ የተሾመ ባሳራሪ
ይመጣና ይለፍፋል
ማን ይሰማዋል
ተሜ ፉጨቱን ቀጥሏል ::

እባካችሁ ተማሪዎች ችግሩን ደርሰንበታል
በተቻለ መጠን ባጨር ጊዜ ይቀረፋል
አሁንም ይፋጫል ማን ይሰማዋል
አስተዳዳሪው ተማሮ
ተመለሰ ወደ ቢሮ
ማፈሪያ ነሆለል
ችግሩን ደርሶበት ሞቷል !

በተሜ ቤትማ
የተፈለገው የራብ አድማ
የወገን ብሶት ሊያሰማ
ወኔ እየፈነቀለው
አሳራሪውን መተናነቅ እያሰኘው
ሲያየው ዙሪያው ገደል ቢሆንበት
አሳራሪውን የሚወጋበት
በተገኘው ሊወናጨፍ
የራብ አድማ አውጆ እርፍ !

የራብ አድማ ስሪቱ
መቁረጫው ስለቱ
ሆኖ ወዳራሪው
የበለጠ ጎዳው ::

እዚህ ላይ ነው ክፋቱ
የራብ አድማ ብልሽቱ
አሳራሪ አለመጉዳቱ ::

የሚሻለው ባያደማም የሚያደብነው
ባያሳርርም የሚያምሰው
ድንጋይ መወርወሩ ነው
እስከሚደርስ ማሳረሪያ ጊዜው ::

መስከረም 22 , 2001 ዓመተ ምህረት

No comments:

Post a Comment

Blog Archive