Thursday, March 14, 2013

"ልሂቃንነት" ? "ሕዝባዊነት?"

ይሄኛው ጽሁፍ ትላንትና 'ፌስ ቡክ' ላይ ላጋራሁት ሃሳብ ትችት ለሰነዘረ የ 'ፌስ ቡክ ጓደኛ'' የሰጠሁት መልስ ነው። 
ግል ለማድረግ ያህል በእስራኤል ሃገር የ"ቁንጂና ውድድር" አሽናፊ የሆነችውን ትውልደ ኢትዮጷዊ ወጣት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ከባራክ ኦባማ ጋር ራት ስለጋበዛት አንድ የእንግዚዝ ጋዜጣ የሰራውን ዜና ብዙ ኢትዮጵያዊ በመደነቅ ሲቀባበሉት ሳይ ግነቱን እና አንድምታውን ግምት ውስጥ በማስገባት ፌስ ቡክ ላይ ለሰነዘርኩት ሃሳብ የተሰጠውን ትችት መልስ ለመስጠት ያህል ነው።  አስተያየቱ እንዲህ ይላል ፡-

"ድሜጥሮስ ደሞ ታበዛዋለህ እንኳን እሷ ልደቱ አያሌው እድሉን ቢያገኝ ጥሩንባውን አንችለውም:: ምነው አንተ critical thinker ብለህ ያልካቸው እንኳን እንደ ግብዳ ስኬት እንደዚህ አይነት ፎቶ ሲለጥፉ አልነበር By the way ain't it a big deal for a 21 years old girl won a pageant and invited to have a dinner with the head of states of US?" 
  
የኔ መልስ ፡-


ጁኒየር - እንዲህ ባለ ጉዳይ ላይ ማብዛት ችየ ባበዛው እና ባባዛው እንዴት ደስ ባለኝ። ነገር በምሳሌ እንዲሉ አጠር ያለ ምሳሌ ልወርውር። ትላንት የተመረጡት የካቶሊክ ጳጳስ ዛሬ መሄድ ወደሚፈልጉበት ቦታ ሊወስዳቸው የተዘጋጀው ደልቃቃ ሊሞዚን ምቾት ስለነሳቸው (የህሊና) "እንዲህ ያለ ነገር አያስፈልግም። ያኛው መኪና በቂ ነው" በማለት ወዳልተንደላቀቀው (ለነገሩ ያልተንደላቀቀ የመሰላቸው ራሱ የተንደላቀቀ ሊሆን ይችላል። የህሊና ሙግታቸውን ግን ልብ ይሏል!) መኪና አመሩ። ዛሬ ስለሳቸው ባየሁት የዜና ትንታኔ ጎልቶ የወጣው ይሄው ሊሞዚን እምቢ የማለታቸው ነገር ነበር። ዜና ሆነ! ፋይዳው ግን ዜና መሆኑ ላይ አይደለም። ፋይዳው በዚህ ድርጊታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ነው። ድሎት ለለመዱት የቫቲካን ቤተኞች እና ለሰሚውም ጭምር የሚለው ነገር አለው። "exclusivity" እንደ ስኬት ለሚቆጥር፣ ትህትና ለሚጎድለው፣ ለደልቃቃ ኑሮ ሲል ለሚሞት እና ለሚገል የህብረተሰብ ክፍል እና ተከታዮቹ - መልዕክት አለው። ሰውየው ሊሞዚኑን ቢጠቀሙ ኖሮ የተለመደ(ኦርዲናሪ) ነገር እሱ ስለሆነ ብዙ ቁብ ባልተባለ ነበር። ( በነገራችን ላይ ድርጊታቸው ስለሰውየው መንፈሳዊ ህይወት ብቻ ሳይሆን ስለመጡበት ማህበረሰብ ማህበራዊ አስተሳሰብ የሚጠቁመው ነገር አለ። አርጀንቲናውያን ለማህበራዊ ፍትህ ያላቸው ግምት ጠንካራ ስለሆነ ይመስለኛል መንግስትን በቋፍ ላይ የሚያኖሩት። መንገድ ላይ ወጥተው መንግስት ሳይገለበጥ እንመለስም ብለው ስርዐት ቀይረው የሚገቡ ናቸው። እንደ ቸ ጉቬራ ያለው ቅን እና ገራገር የፓለቲካ ሰው የወጣውም ከዛው ማህበረሰብ ነው) የሆነ ሆኖ የሰውየው የወደፊት ሁኔታ እንደሚቀጥሉበት ወይ እደማይቀጥሉበት (ሪዛይን ያደርጉም እንደሆነ) የሚታይ ነው።

ወደ ቁንጂና ውድድር አሽናፊዋ ጉዳይ ስለመለስ- ልጂቱ ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሽሞን ፔሬዝ ቤት (ወይንም ቢሮ እርግጠኛ እይደለሁም) ተደውሎላት በሰውየው መኖሪያ ቤት ከኦባማ ጋር እራት እንድትበላ ስትጋበዝ እሽ በማለቷ ወይንም ጉዳዩን በማስመልከት ምናልባት ላናገሯት የእግሊዝ የሜዲያ አሰተያየት መስጠቷ ምንም ችግር የለውም።(በነገራችን ላይ ፕሬዝዳንት ባይሆን ኖሮ የማያቃት ሰው ደውሎ እቤቴ ራት ብይ ቢላት ትሄድ ነበር? እንደዛ ካደረገችማ ኢትዮጵያዊ እይደለችማ። ጎንደሬነቷስ የታለ ማስባሉ አይቀርም። ሃሃ)። ችግሩ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ (ያውም ተማረ የሚባለው)ዜናውን እንደትንግርት አይቶ እንደ ዱላ ቅብብል እየተቀባበለ ላይክ ሲያደርገው ማየት ስለ ፖለቲካ ብስለታችን እና ስለ ነጻነት ስላለን ግንዛቤ እንድጠይቅ ያስገድዳል። ነጻነት የእሳቤ ብቻ ሳይሆን የእኗኗር ዘየም ውጤት ነው። ነጻ ለመሆን የሚፈልግ ትውልድ እና ሕዝብ ዓለምን እና ህይወትን ሳናውቀው እንደዋዛ ነጻነታችንን እንድናጣ ቀላል የማይባል አስተዋጾ ባበረከቱ አደንዛዥ ማህበራዊ ልማዶች እና አስተሳሰቦች ብሎም እያዋዙ እያስመሰሉ ሲያስፈልግ ደሞ በጉልበት በሚገዙን ሰዎች የዓለም እይታ ዓለምን የሚያይ ከሆነ ነጻ የሆን እድሉ የመነመነ ነው። የነጻነት ጥንስሱ የለማ። ነጻነት ከንቃት ህሊና ለንቃተ ኅሊናው ጋር መሳ ለመሳ ከሚሄድ የአኗኗር ዘየ የሚወለድ ጉዳይ ነው።

ሲጀመር የ"ቁንጂና ውድድር" የሚባለውን ሃሳብ ከቁምነገር የማልጽፈው ጉዳይ ነው። የ"ቁንጂና ወድድር" ውጤት ደሞ እንዲህ የፓለቲካ ሰዎችን ግምት(በድንገት ሳይታሰብ የሆነ ነገር እይመስለኝም) አግኝቶ የዜና ሽፋን እንዲሰጠው ሆኖ ሲቀርብ መታየት ያለበት እንዲህ ባለ ፕሮፕጋንዳ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው? በመጀመሪያ ይሄ ታሪክ ስለ 'ኤሊቲዝም' ነው ስለ 'ህዝባዊነት' የሚተርከው? ኮንፎርሚስቶች ( መስሎ አዳሪዎች) ዲዛይንድ' በሆነ “ሶሻል ሞቢሊቲ” - ለ'ልሂቃኑ' ቅርበት እንዲኖራቸው ሲደረግ የሚዳነቀውን ያህል ስርዐቱን ያልተቀበሉት (“ዲሴንት የሚያደርጉት”)  በየቦታው በተቸከሉ ማህበራዊ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችካሎች ጋር እንዳይንቀሳቀሱ ተደረገው የታሰሩ ሚሊየኖችም አይታወሱም። አይዘከሩም። ስደተኞች ላይ ያለው ትርፍ ከጉልበት ዋጋ (“ከሌበር ቫሊዮ”) ጋር የተሳሰረ ብቻ አይደለም። "አይዲዮሎጂካል" ሊዮም እንዲኖራቸው ይፈለጋል። ምናልባት የምዕራቡን ዓለም አስራር አይተኽው ይሆናል።

ዜና ፣ ዶክመንታሪ፣ቃለ መጠየቅ ወይንም ሌላ ታሪክ ሲስራ በውስጡ የርዮተ-ዓለም ትርፍ እንዲኖረው ተደርጎ በብልጠት ስለሚሰራ ለማያቅ ሰው እውነቱን ከውሸት ፣ ግነቱን ከሚዛናዊ ዜና ለመለየት ያስቸግር ይሆናል። እንዲህ እንድልጂቱ ባለው ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ስዎችን (ያውም የዓለም መሪዎች የሚባሉትን) ትኩረት አግኝቶ ሲሰራ - ልጂቱ ብታውቀውም ባታውቀውም ማውራት የተፈለገው ስለ "ስኬት" እና "ዕድል" ብቻ አይደለም። ታሪኩ የ"ኮንፎርሚቲ '(መስሎ እንዳረጉት ሆⶈ የማደር) ታሪክ ነው ወይንስ የጥረት እና የትግል? "ኮኦፐሬቲቭ" የመሆን ታሪክ ነው? ስ ቡክ ላይ እንዳልኩት ከእስራል በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ላይ ስለሚደረሰው የሚንሰማው ነገር የተለየ ነው፡፡ ጭራ በቅርቡ ኢትዮጵያውያኖቹ እንዳይዋለዱ ያለ ዕውቀታቸው የማምከኛ ክትባት ይከተቡ እንደነበር ሰምተናል። የእስራኤልም ባለስልጣናት ጉዳዮን አምነው በይፋ ይቅርታ ጠየቁበት የተባለ ጉዳይ ነው። ልጂቱ ተሳካላት የሚባለው እንግዲህ እንዲህ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ከዚህ የ"ስኬት" ዜና ጀርባ እና ከተሰጠው የዜና ሽፋን ከዚህ በፊት ከነበረው ተሞክሮ በመነሳት መውሰድ ያለብን ግምት አለ።

ልጂቱ በልጂነት አቅሟ ደረሰብኝ ያለችው ነገር አስባ፤ የተደረገላት ጥሪ እንዲፈጥር የታሰበውን አንድምታ ገብቷት ያንን ግምት ውስጥ አስገብታ  ግብዣውን ባትቀበል እና  አለመቀበሏ  ዜና ቢሆን ኖሮ ታሪኩ ከ 'ኢሊቲዝም' የበለጠ የህዝባዊነት ታሪክ ይሆን ነበር። የተለመደ እና የሚጠበቅ (ኦርዲናሪ) ከመሆን ይልቅ ያልተለመደ እና አስተማሪ ሊሆን ይችል ነበር። እንዳልኩት በልጂቱ ለመፍረድ እይደለም። ንቃተ ህሊና ከዕድሜ ጋር ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ማህበረሰባዊም መሰረት አለው። (ለነገሩ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ከልጂቱ ብዙ በማይርቅ ዕድሜ ክልል ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነጻነት እያነሱ የሚጥሉ እና ክህዝባዊ ሃሳብ ጋር የሚኖሩ እንዳሉ ፍንጮች የሚታዮ ይመስለኛልእንዳናደናግራቸው እንጂ)። ማህበራዊ ንቃት ህሊና ቢ
፣ጠንካራ የነጻነት ስሜት እና ነጻነት ለማግኘት ትጋት ቢኖር ልጂቱ ያለችበት ዕድሜ ብርቱ የለውጥ ፈላጊነት እና የአርበኝነት ስሜት የሚስተዋልበት ዕድሜ ነው። ነገሮችን ለማገናዘብ የሚያንስ ዐድሜ አይደለም። በታሪክ የምናውቃቸው የታላላቅ አብዮቶች ሞተር የሆኑት በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ዜጎች   እንደሆኑ መዘንጋት አያስፈልግም። የሆነ ሆኖ እንዳልኩት ልጂቱን ነጥሎ ለመተቸት ወይንም አገኘሁ የምትለውን 'ስኬት' ለማሳነስ ወይ ለማጣጣል ሳይሆን የኔ ጉዳይ በማህበረሰብ ድረጃ ዜናውን እየተቀባበልን የተረዳንበትን መንገድ ለመተቸት ነው። ነጻነት ፈላጊዎችም የነጻነት ትርጉም እና ፋይዳ የገባቸውም ሰውችም አያስመስለንም።  የምንጋራቸው እና የምናጋራቸው ሃሳቦች ለንቃተ ህሊና መዳበር እና ለነጻነት ለሚደረገው ትግል ያላቸውንም ሚና ግምት ውስጥ ማስገባ የሚያስፈልግ ስለሚመስለኝ ነው።

በመጨረሻ እኔ የማደንቃቸው "critical thinker" እነማን ናቸው? እሱን እብራራ እና እመለስበት ይሆናል እንደሁኔታው።


_________________________


 ወድ አንባቢያኖቼ- ቦርከና ብሎግን ወደ ዌብ ሳይት ለመቀየር እየሰራሁ ነው።   በቅርቡ ያልቃል ብየ እጠብቃለሁ። ስራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አሳውቃለሁ። በ'ፌስ ቡክ'ም ቦርከና የራሱ ገጸ-ተከፍቶለታል።  መከታተል ለምትፈልኩ ይሄን ሊንክ ተከትላችሁ ማግኘት ትችላላችሁ።   https://www.facebook.com/pages/Borkena/294762583969356?ref=hl

No comments:

Post a Comment

Blog Archive