Monday, June 27, 2011

በማንነታችን ላይ የተጋረጠ ፈተና

ትንሽ ቀደም ባለው ዘመን የመንግስትን ተፈጥሮ አና አስፈላጊነት ለማስረዳት ጠለቅ ያለ እሳቤ ያደረጉ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ አሳቢዎች (Political thinkers) የመንግስትን አደረጃጀት እና በህብረተሰብ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ለመተንተን ከሰው ልጂ ተፈጥሮ ነው የጀመሩት:: የሰውን ልጂ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጂ በህይወት ዘመኑ የህይወት ግብ ሊሆን ስለሚገባው ነገርም ሀሳብ ሰጥተዋል:: እነዚህ አሳቢዎች በሰው ልጂ ተፈጥሮ ላይ የበነራቸው አመለካከት እንደሚለያየው ሁሉ የሰው ልጂ በህይወት ዘመኑ እንደ ግብ እና የህይወት መርህ ሊይዘው ይገባል በሚሉትም ነገር ላይ ልዮነት አላቸው:: እንዳንዶች ( እንደ ጆን ሎክ ያሉ) መኖርን ወይ አድሮ መገኘትን (preservation of life ብለው የገለጹትን ) እና ቁሳዊ ብልጽግና የሰው ልጂ ዋነኛ የህይወት ግብ ነው የሚል ሀሳብ ሲያራምዱ ሌሎች ደሞ ሰውን ሰው የሚያደርገው እንደ እንስሳ አድሮ መገኘት እና የእንስሳዊ ህይወት መኖር ሳይሆን ስው ለክብሩ መኖር እና ለዛም እውቅና (recognition) ለማግኘት ህይወቱን እስከሚያጣም ድረስ ቢሆን ሲታገልለት ነው የሚሉ ነበሩ (ሄግል በዋነኛነት ይጠቀሳል):: በኍለኛው አስተሳሰብ መሰረት ምንም ያስከትል ምን (-ሞትን ጨምሮ ) የሰው ልጂ ትግል መሆን ያለበት ስብዕና እና ክብር ላለው ይህወት ነው:: እንደ እንስሳ መኖር እና ቁሳዊ ሀብት ማፍራት ትርጉም የለውም :: የሰው ልጂ ስብዕናው እና ክብሩ እውቅና ባልተሰጣቸው ሁኔታ ትግሉን ማቆም የለበትም የሚል አስተሳሰብ ላይ ያተኩራል::

ቁሳዊ ሀብት ብቻ ማከማቸት የህይወት ትርጉም እና ግንዛቤ መነሻ እና መድረሻ ባልነበረበት - የካፒታሊዝም ስርዐት የምርት ሂደቱን በማስፋፋት የሚመረተው ምርት በሙሉ ተጠቃሚ እንዲያገኝ የተጠቃሚ ማህበረሰብ የመፍጠሪያ ዘዴ ሳይስፋፋ እና ሰዎች የማያስፈልጋቸውን ነገር ልክ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲያምኑ እና እንዲገዙ ከመደረጉ በፊት- ከመሬት ሌላ ለሌሎች ሀብቶች ብዙም በማይማለልበት ፊዎዳላዊ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ክብር ትልቅ ቦታ ነበረው:: ""ክብር"" በቁሳዊነት ላይ የሚያተኩረውን ሀሳብ ለሚያራምዱት የማይጨበጥ የማይዳሰስ የማይኖር - አዲያሊስት ነው ይሉታል:: የጀነት ወይንም የመንግስተ ሰማያት ሀሳብ ሰዎች የሚኖሩለት በአይን ስለሚታይ ወይንም በእጂ ስለሚዳሰስ አይድለም:: በተመስጦ ; በእሳቤ እና በእምነት ስለሚታይ ነው:: ነብዮ መሀመድ የደረሰባቸው ነገር የደረሰባቸው ለእምነት ነው:: የክርስቶስ ተከታዮች የሞቱት ለእምነት ነው:: በሩቅ ምስራቅ የተነሱ ሌሎች የእምነት መምህራን የደረሰባቸው እንግልት የደረሰባቸው ለእምነት ነው:: ቅጥ ያጣ የማቴሪያል ፍላጎትን መቆጣጠር እና ለክብር ቦታ መስጠት በተወሰነ መልኩ መንፈሳዊ ገጸታ አለው ብየ አስባለሁ:: እንደገባኝ በየትኛውም እምነት ከልክ ያለፈ ስግብግብነት እና ማቴሪያል የማከማቸት ፍላጎት አይበረታታም:: ክብርን እና የሰውነት ትርጉምን በማጣት የሚገኝ ሀብትም ሆነ መሰንበት የሰውን ልጂ ደስተኛ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን :: ለማቴሪያል የሚኖር ማህበረሰብ ግለኛ እና የተበታተነ ነው:: ለሀሳብ እና ለእምነት ( ማህበራዊ; ባህላዊ; ሀይማኖታዊ ) የሚኖር ማህበረሰብ ደሞ ማህበራዊ አስተሳሰብ ያለው ለወንጀል ሆነ ለስግብግብነት ሆነ ሀገር ለመክዳት ሆነ እና ለሌሎች መጥፎ አንድምታ ላላቸው ማህበራዊ ደዌዎች መሰረት ሊሆን አይችልም:: በእንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ የጋራ የሆነ የሚከበር ማህበረሰባዊ ህግ ስለሚኖር ነውር ;ወንጀል እና መሰል ነገሮች ቦታ አይኖራቸውም:: ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ከታደሉት ውስጥ አንዷ ነበረች:: እነዚህ ነገሮች ከማህበራዊ ህግጋትም አልፈው ባህልም ሆነው ነበር:: በቅርቡ የምንሰማቸው የተማሪዎች ሴተኛ አዳሪ መሆን ; የወንጀል መበራከት ; ስግብግብነት በወንጀል እና ዘረፋ ለሚያምን የፖለቲካ ቡድን ተባባሪት የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር ከማህበራዊ ማንነታች ምን ያህል እያፈነገጥን እንደሆነ ነው:: በእንደዚህ አይነት ሁኔታም ጸሀፍቶች የሚተቹን የኢትዮጵያን ባህል ነው::
አሁን አሁን የተነሱ ጸሀፍት ብዕራቸው የኢትዮጵያን ባህል እና ታሪክ ለመተቸት የሚነቃውን ያህል ኢትዮጵያን በነጻነት ጠብቆ ለማቆየት የተደረገውን ትግል እና ማህበራዊ እሴቶቻችንን ( ለምሳሌ እንደ ይሉኝታ እንደ ክብር እንደ ነግበኔ የሀገር ፍቅር ያሉ ነገሮችን) እና የህይወትን እይታ ጭምር በስከነ መንፈስሊመረምሩ ሲፈልጉ አይስተዋሉም:: በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያዊ በባህል ላይ አመጽ ለማቀጣጠል የሚፈልጉ ኢትዮጵያ ሶስት ሺ ዘመን ተኝታለች ብለው የሚያስቡ አይጠፉም:: እርግጥ ነው ባህል እና እና ማንነት ማህበራዊ ስሪት (social construction) ነው:: የኢትይጵያን ማህበረሰብ በታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ሆነ ; ማህበራዊ ስሪት የፈጠረውን ኢትዮጵያዊ ባህል እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ከውጭ ሀይሎች ጥቃት ጠብቆ ለማቆየት የተደረገውን ትግል ስናይ- በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ""የህይወት ትርጉሙ ነብስን ማቆየት እና ሀበት ማፍራት እንደ እንስሳ መኖር"" የሚለው አስተሳሰብ ቦታ እንዳልነበረው እንረዳለን:: ይልቁንም በኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ የነበረው አይዲያሊስት እይተባለ የሚጣጣል ነገር ግን በህይወት ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው ""ሰው ያለ ክብሩ ምንድን ነው?”"" የሚል አስተሳሰብ ነበር:: የኢትዮጵያ ክብር ነጻነት እና አንድነት ተጠብቆ ሊቆይ የቻለው ለክብር ; ለነጻነት እና ለአንድነት ክፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ወደ ባህል የተቀየረ ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ስለ ነበረ ነው:: የሰው ልጂ ስብዕና እና ማንነት መመዘን ያለበት ለክብር በሚሰጠው ቦታ እንጂ ለስግብግብነት እና ስግብግብነት ለሚወልደው በወንጀል ላይ ለተመሰረተ ክብረት አን ሀብት መሆን የለበትም:: አልነበረምም በታሪካችን:: ከዚህ ጋር ተያዮዞ ነው - ነውር; ይሉኝታ ነግበኔ እና ሌሎችም ማህበራዊ ዕሴቶቻችን የማህበራዊ ህግጋታችን መስፈሪያዎች የነበሩት:: የክብር እና የመከበር ነገር የሚገባው ዜጋ ለነውር እና ለይሉኝታ ይገዛል:: ምክንያቱም ነውርን እና ይሉኝታን ሲረሳ የሚጎዳው ክብሩን ስለሆነ:: በጋራ የተፈጠረውን ማህበራዊ ህግ ( ይሉኝታን እና ነውርን ጨምሮ) የሚያከብር ራሱን ያከብራል:: ለክብር የመሞት ነገር መሰረቱ የተተከለው በዚህ መልክ ነው:: የጀግንነት መሰረቱ የሚወሰነው ለክብር በሚሰጠው አመለካከት ነው:: በፆታ ግንኙነት እንኳን አፍቃሪ የእጮኛውን ልብ የሚገዛው በክብሩ ላይ የማይደራደር ሲሆን ነው:: ይቀነቀን የነበረ '' ወይ ግደልላት ወይ ሙትላት የፈሪ ወዳጂ አታስብላት"" ለጀግንነት እና ለክብር የሚሰጥ ዋጋ ነጸብራቅ ነው::

ይሄ ማህበረሰባዊ ክብር እና ማህበራዊ ህግ የሀገርም መለያ ነበር:: በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ላይ እንደሚሰነዘር ጥቃት ነው የሚለውን እምነት ኢትዮጵያውያን በተግባር ኖረውታል:: እንደዛ ባለው ዘመን ኢትዮጵያ ወረራ በተቃጣባት ቁጥር ኢትዮጵያውያን ለመግደል ወይ ለመሞት ነው የሚያኮበኩቡት:: ከእንደዚህ አይነቱ ተጋድሎ ራሱን የሚያገል ማህበራዊ ተቀባይነት አልነበረውም:: በዚያን ዘመን እናቶች ልጆቻቸው የሀገርን ክብር ለማስተበቅ ለዘመቻ ሲነሱ እንደኛ ዘመን እናቶች አትሂድብኝ ትሞትብኛለህ አይሉም:: ይልቁንም ስንቅ አደራጂተው በደስታ ይቅናህ ቀኙን ይስጥህ ብለው መርቀው ይሸኛሉ:: የበረቱትም ይከተላሉ:: የኢትዮጵያን የታሪክ ማህደር ስናገላብጥ ትልቅ ታሪክ ያስመዘገቡት አንድ ለናቱዎች ሆነው የምናገኝበትም ሁኔታ አለ:: ሚስቶችም በእንደዚህ አይነት ጊዜ ባሎቻቸውን አበረታተው ይሸኛሉ:: ይከተሉማል:: ይሄ እንግዲህ አንድም ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ትስስር እና ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን የነበራት ቦታ የተከበረ እና የተወደደ በመሆኑ ነው:: አንድም ኢትዮጵያውያን ለህይወት እና ለክብር ይሰጡት የነበረው ትርጉም ጥልቅ ስለነበረ ነው:: አፄ ቴዎድሮስ የራሳቸውን ህይወት የወደሱብት እምነት አስብ እንደነበረው ምን አይነት ወንድ ነው ክንዴን ሳልንተራስ ክንዴን የሚጨብጠው ከሚል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ንጉስ አይማረክም ከሚል ለኢትዮጵያም ከነበረ ጥልቅ አክብሮት እና ፍቅርም እንደነበር አንድ ጓደኛየ በቅርቡ አጫውቶኛል:: ይሔም ለነፃነት እና ለሀገር የነበረ አስተያየት ቀናኢነት ብቻ ሳይሆን ለህይወትም ይሰጥ የነበረውን ፋይዳ እና ትርጉም ያመላክታል::የአልሸነፍ ባይነቱ ሚስጥር በህይወት ትርጉም ላይ ከነበረ ጥልቅ እይታ እና ጥርት ያለ አቋም የመነጨ ነበር:: ኢትዮጵያ (ከፈጣሪ ጥበቃ መልስ) ነጻነቷ ተከብሮ የቆየበት ሚስጥር ይሄው ነው:: የኢትዮጵያውያንም ምኞት እና መፈክር ""ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!"" የሆነበትም ምክንያት ይሄው ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተተከሉ እና ተቀባይነት እያገኙ የመጡአዳዲስ ማህበራዊ አስተሳሰቦችን እና ልማዶችን ግምት ውስጥ በማስገባት እውነት ""ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች ወይ?"" ወይንም ""ለዘላለም የምትኖርበት ሁኔታ አለ ወይ?"" ብለን ስንጠይቅ ትንሽ ስጋት የሚጋርጡብን ሁኔታዎች ያሉ ይመስለኛል:: አለን እንል የነበረው ነገር ባህል እና ማህበራዊ እሴት ነበር:: ነውር; ይሉንታ ; የሀገር ፍቅር እና በሀገር ላይ ልክ ያልሆነ ነገር ሲደረግ የመጠቃት; የመቆጨት እና የመቆጣት ስሜት ነበር:: በታሪክ ኢትዮጵያውያኖች በጭፍን ነገስታቶቻቸውን የሚከተሉ አልነበሩም:: ንጉስ ተቀባይነት(legitmacy) የሚያገኝባቸው መሰረታዊ ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ በመካከለኛው ዘመን አውሮፓውያን የጎንደር ነገስታቶችን አማለው እነሱን ካቶሊካዊ ካደረጉ መላውን ኢትዮጵያን በቀላሉ ካቶሊካዊ ማድረግ እንደሚቻል ያምኑ ነበር:: ያሰቡትንም ሞከሩት:: የተወሰኑ የጎንደርን ነገርታቶች ቀየሩ:: ነገስታቱም የተቀበሉትን አዲስ እምነት በኢትዮጵያውያን ላይ ለመጣል አዲስ አካሄድ ጀመሩ:: የተከተለው ነገር ግን ቁጣ እምቢተኝነት እና ጦርነት ነበር:: ነገስታቱም ተሳስተው እንደነበር አምነው ሕዝብ አሸነፈ::

ከላይ እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት ወይንም ኢትዮጵያን ከሌላው ማህበረሰብ የሚለያት መልከዐምድራዊ አቀማመጧ; እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች ብቻ አይድሉም:: ማህበራዊ ስሪቱ እና በዘመናትየተገነባው ባህላዊ እኛነታችን ነው ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያህብላት::ኢትዮጵያ ቀጥላለች የሚባለው ይህ በዘመናት የተገነባ እና ብዙ ኢትዮጵያውያን በህይወት የከፈሉበት እሴት ቀጥሎ ከሆነ ነው:: ለምሳሌ ለኢትዮጵያ ያለ ፍቅር እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለ ትስስር; ማህበራዊ ህግጋቶቻችን ( ነውር; ነግበኔ ) እና ሌሎችም:: ክብሩን እና የሀገር ፍቅሩን በመኖር የማይቀየርባት በነበረች ኢትዮጵያ ማን ኢትዮጵያዊ ወጣት በስራ ዕድል እና ሌሎች መደለያዎች መሰሪ ለሆኑ ሀይሎች ጋሻ አጃግሬ ይሆናል ብሎ ያስብ ነበር? ነውር እና ክብር የማህበራዊ ተቀባይነት መሰረት በነበረባት ኢትዮጵያ ማን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሴተኛ አዳሪነት ይሰማርሉ ብሎ ያሰበ ነበር?? ማን በኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶችን እርቃናቸውን እና ሀፍረታቸውን በእግዚቢሽን መልክ እያሳዮ ገንዘብ የሚቀበሉበት ዘመን ይመጣል ብሎ የገመተ አለ? ማን ግብርና እና ገበሬነት ላብዛኛው ህዝብ መተዳደሪያ በሆነባት ኢትዮጵያ አንድ አገር የሚያክል የኢትዮጵያ መሬት ለውጭ ቱጃሮች ሲቸበቸብ ያለ ቁጣ እና የለ ንዴት በዝምታ እና በግዴለሽነት የሚያይ ትውልድ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጠራል ብሎ የሚያስብ ነበር?? (አሁን “”ያልታረሰ እና አይን አይኑን ሲታይ የነበረ መሬት ነው”” እየተባለ ለውጭ ኢንቬስተር እየተሰጠ ያለው መሬት የኢትዮጵያ ነገስታቶች በቅኝ ግዛት ይዘው በዝብዘውታል ሲባል የነበረ የኢትዮጵያ ክፍል ነው:: )ማን ኢትዮጵያውን ነብሳቸውን እስከሚስቱ ድረስ ከሚወዱአት አገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር የላላ እና የይስሙላ ይሆናል ብሎ የገመተ ነበረ?? በጥቂት አስርት አመታት ውስጥ የተከሰተው ይሄ ሁሉ ውጥንቅስ የምን ውጤት ነው?? ማህበራዊ ህጋችንን የሰባበረው ማን ነው?? በምን አይነት ዘዴ?
ምንም እንኳን ከውጭም ከውስጥም በረቀቀም ባልረቀቀም መንገድ ኢትዮጵያውያ አሁን እየሄደችበት ወዳለው ማህበራዊ ቀውስ እና ማንነት የማጣት መስመር ለመውሰድ የተጉ እና አሁንም የሚተጉ ሀይሎች ቢኖሩም : የሆነው ነገር ሁሉ ግን የሆነው ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ብለን የምናስብ ወገኖች አደጋውን በጥሞና ተረድቶ ኢትዮጵያን ለዘላለም ለማኖር የሚያስቺል ስልታዊ እና የተቀናጀ አካሄድ ለመሄድ ባለመቻላችንም ነው:: የኢትዮጵያ ጠላቶች ብርታት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንም ድክመት ነው የችግሩ ምንጭ:: የኢትዮጵያን ለዘላለም መኖር ለማረጋገጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደሩረጉ ያሉትም ያንን ዐላማ በማሳካት ረገድ ባህል የሚፈጥረውን ጉልበት እና አቅም የተረዱት አይመስሉም:: እንደውም ለተጨቋኝነታችን ምክንያቱ ባህል ነው ብለው የሚያስቡም አይጠፉም:: የኢትዮጵያ ባልህ ባይተዋር ሆኖ እንደባላንጣ የሚታይበት እና ላለመሰልጠናችን እንደምክንያት የሚቆጠርበትም ጊዜ አለ::

አንግዲያውስ ኢትዮጵያ ለመታደግ ትርጉም ያለው ስር እንስራ ካልን የባህልን ግብዕትነት ተጠቅመን ወጣቱ ከማንነቱ እና ከባህሉ ጋር በአክበሮት እና በፍቅር የሚኖርበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል:: ይሔንን ለማድረግ ብዙ አማራጮች አሉ:: አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ቡድን ድንጉጥ ባህሪ ስላለው እሱን በማያስደነግጥ እና ሌላ እርምጃ ለመውሰድ በማያነሳሳው መልኩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በመላው ኢትዮጵያ በባህላቸው እና በሀገራቸው ላይ የሚወያዮበትን እና የሚመክሩበትን የራሳቸውን መድረክ እንዲፈጥሩ እገዛ በማድረግ መጀመር ይቻላል:: ኢትይጵያን ለማዳን መጀመሪያ ማህበራዊ ቤዝ መፍጠር ያስፈልጋል:: ይሔንን ለማድረግ ደሞ የማህበራዊ ቆሻሻውን የሚያጽዱ እና የሚያጸዱ ሌሎች ጋሽ አበራ ሞላዎች ያስፈልጋሉ:: በዲያስፖራ የምንገኝም ይሄንን በማገዝ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት እንችላለን ማድረግም አለብን:: የኢትዮጵያ ምሁራኖችም ኢንተሌክቹዋል እንቅስቃሴ መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል:: በኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ላይ በሰከነ መልኩ ሪፍሌክት ማድረግ አልጀመርንም ባይ ነኝ:: ቻይናዎቹ የአንድ ሺ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል ነው የሚሉት:: የምንጀምረው እርምጃ ግን በትክክለኛ አቅጣጫ መሆነ አለበት:: በተሳሳተ አቅጣጫ ጉዞ ከተጀመረ አለመድረስ ብቻ አይደለም ያለው አደጋ::

Monday, June 13, 2011

የልብ እግር ሲሰበር ...ሲሽር

የልብ እግር ሲሰበር
ዓላማ ፣ ተስፋ ፣
ፍላጎት ፣ ምኞት... ሀሴት
ሕይወት አልባ ይሆናሉ::
ሲሽር እንደ አዲስ ነብስ ይዘራሉ ::
ህብረት ይፈጥራሉ
መሰናክል ይዘላሉ ::
ግና ሰባራ ልብ የሚያራምደው
...ወጌሻው
የጽናት እና የእምነት ትብብር ነው ::

ሰኔ 7, 2003,
ቶሮንቶ

Blog Archive