Friday, April 20, 2012
""ሁሉ አይጠየቅም::" "ሁሉ አይነገርም::"...?
""ሁሉ አይጠየቅም::"" ""ሁሉ አይነገርም::"" የሚለውን እሳቤ ወደ ልቤ ልወስደው እልና ታዲያ እንዴት መማማር ወይ መግባባት ይቻላል የሚል ነገር ይመጣብኛል:: ያለ ንግግር በምልክክት መግባባት ቢቻል አንዳንዴ ንግግርን ማስቀረት እርግጥ ይጠቅም ይሆናል:: አይቻልም::
ሰው የሚናገረው ወይ የሚጠይቀው ነገሮችን ለመለወጥ ወይንም መልስ አገኛለሁ ብሎ አምኖም ላይሆን ይቻላል::ጥያቄው እንደጥያቄ መሰንዘሩ ወይ ደሞ መነገር የለበትም ተብሎ የሚታሰበው ነገር በመነገሩ ከእፎይታ ስሜት ባለፈ ; ነገሮችን ለሰው ከማካፈል ስሜት ባለፈ ; ጥያቄየን ወይንም ሀሳቤን በግላጭ ማውጣቴ ቢያንስ ባጋጣሚ ካለማወቅ እና ከግንዛቤ እጥረት የመጣ እንኳን ቢሆን የመማር ዕድሉ ይኖረኛል ብሎ ከማሰብም የመነጨ ነው::
ሰላማዊ ሰልፍ የሚባል ነገር ከወጣሁ ሰንብቻለሁ:: ጊዜ አጥሮኝ ወይ መገኘት ሳልችል ያልተገኘሁባቸው ግን ጥቂቶች ናቸው:: ብዙ ጊዜ የማልሄድበት ዋነኛ ምክንያት የሚያስቆጣን በሀገር ላይ የሚቃጣ የህወሀት ጥቃት እዚህ ውጪ ሀገር በሚደረግ በፔቲሺን እና በሰላማዊ ሰልፍ ይቀየራል ብየ ስለማላምን ነው:: ምንም ያህል እውነት ብንይዝም ምንም አይነት የፍትህ ጥያቄ ብናነሳም በዓለማችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንደምናየው የዐለም ዓቀፍ ፖለቲካ በመርህ እና በፍትህ የተመሰረቱ ናቸው ብየ ስለማላምን ነው:: በታሪክም ይኸው ነበር ሁኔታው:: አሁን ባለንበት ዘመን ደሞ ችግሩ እየከፋ መጥቷል:: አንዳንዴ እንደ ህወሀት ያለ ቡድን በቀዳሚነት ቅጥ ያጣ ዓለም አቀፍ ርዳታ ተጠቃሚ የሚሆነበትን አገባብ አስቤ አስቤ በመርህ እና በፍትሀዊነት ላይ ያልተመሰረተ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ነጸብራቅ ( ወይ አንድ ማሳያ) ከመሆኑ በስተቀር ሌላ ምክንያት አጣለሁ::
ሀገሩን ተቀምቶ እየተዘረፈ በዚያም ላይ በርግጫ እን በጡጫ እየተረገጠ በአፈና ስር ያለው ኢትዮጵያዊን በጥርጣሬ እያዮ ረጋጩን ህወሀትን አንዳንዴ የሚቆጡ እየመሰሉ ርባና በሌለው መግለጫ ሌላ ጊዜ በዝምታ የሚደገፈው ህወሀት ነው:: ምንም እንኳን ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ መደርደር ባልችልም ከማየው ነገር ግን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሀያላን መንግስታቶች ምንም ቢያጠፋ ምንም የህወሀት ነገር አይሆንላቸውም የሚል እሳቤ ላይ እደርሳለሁ:: ከህወሀት የህዝብ ፍቅር አለመኖር እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታዛዢነት ጋር ሊያያዝ ይችል ይሆናል ጉዳዮ:: ቁም ነገሩ ግን ህወሀት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ነገር ሀያላኑ መንግስታትም ሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳምረው ያውቁታል:: የየቀኑ የየዕለቱ ዘገባ አላቸው:: በየአታሸዎቻቸው አማካይነት:: እኛ ታዲያ የሞኝ ፈሊጥ አይሉት ምን አይሉት ልክ እንደማያዉቁ ህወሀት ባወጣው እቅድ ቅደም ተከተል መሰረት አንድ ባንድ ጥፋት ሲያደርስ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እናሳውቃለን እያልን በየከተሞቹ ሰልፍ እንወጣለን:: ልክ እንደማያውቁ:: አልዋጥልህ እያለ ከሰልፍ ያስቀረኝ የነበረው ጉዳይ::
ዛሬ ግን ለራሴ የገባሁትን ቃል-ኪዳን አፍርሼ እንደገና ለሰልፍ ወጣሁ:: የሰልፉ ጉዳይ የዋልድባ ነገር መሆኑ እና ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ክርስቲያኑ ህዝብ እየተሰለፈ ከሰልፉ ቦታ መሰወር ( በስራ ምክንያትም ቢሆን) እንደሌለብኝ ባምንም ሰልፉ የተደረገው በኦንቴሪዮ መንግስት (የአውራጃ አስተዳደር እንበለው) ፓርላማ እንደመሆኑ የዋልድባ ጉዳይ በእርግጥም የኦንቴሪዎ መንግስት ጉዳይ ይሆናል ለዋልድባ ኬር ያደርጋል ከሚል እምነት አልነበረም:: ይሄ መንግስት ለጩኽታችን እጂግ በጣም ትኩረት ከሰጠ ሊያደርግ የሚችለው ጉዳዮ ለሚመለከተው ዩኔስኮ በካናዳ መንግስት አማካኝነት ለህወሀት መንግስት የተማጽኖ ደብዳቤ ይጽፍ ይሆናል --- እንግዲህ "what is there in it for us?" የሚለውን ከመለሱ ማለት ነው:: በሌላ አነጋገር ፊት ለፊታቸው ስለ ዋልድባ ገዳም የሚጮሑ ኢትዮጵያውያንን ገዳም እንዳይታረስ እና የስኳር እርሻ እንዳይሆን የሚታገሉበት ራሺናሊቲ የህወሀት መንግስት በኢንቨስትመት እና ባህል አንፅር ከሚሰጣቸው ጥቅም ራሺናሊቲ ከበለጠ ነው:: ለማንኛውም ባላምንበትም (በሰላማዊ ሰልፍ) መሄድ አለብኝ ብየ ራሴን ሳላሳምነው አዘዝኩት:: ሄጄም ግን አላፈርኩም ጥሩ ስሜት ተሰምቶኝ መጣሁ:: በተለየ ምክንያት ቢሆንም::
ከምንም ነገር በላይ ያስደሰተኝ የተደረገው ጸሎት ነው:: የኦንቴሪዮ ፓርላማ ፊት ለፊት ሆነን "" ስማነ አምላክነ ወመድሀኒነ"" ስንል ተስፋ ባላደርኩብት እና በማላደርግበት ተቋም ፊት ቆሜ የበለጠ መፍትሄ የሚሆን ሀያል አምላክን በዛች ቅጽበት በዛች ቦታ በማስታወሴ ተደሰትኩ::ከምርም ጸሎት አደረኩኝ:: ጸሎቴ ደሞ አግዚያብሄር ሀገር ቤት ላሉ ልባም እና ደፋር ልጆች የበለጠ ድፍረትን እና ማስተዋልን እንዲሰጣቸው እና ቁጥራቸውን ከእለት ወደ እለት እንዲያበዛው ነው:: የሚያባንኑ የሚቀሰቅሱ እና የሚመሩ ኢትዮጵያውያኖች እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠሩ አያሰብኩ ነበር ""ስማነ አምላክነ ወመድሀኒነ"" ያልኩት::
ሁለተኛ ያስደሰተኝ ነገር የኢትዮጵያውያንን ሙስሊሞች ጨዋነት ዛሬም በማየቴ ነው:: ሀጂ መሀመድ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ከእኛ ከክርስቲያኖቹ እኩል ስለ ዋልድባ ሊጮሁ እና ወጣቱ ከተጠመደለት የሀይማኖት እና የዘር መከፋፈል እንዴት ስብሮ መውጣት እንዳለበት ሊያስታውሱ ነበር:: በሰል ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል:: ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ወጣቶችም እንዲህ ያሉ ናቸው:: እውቅና እና መቻቻልን የሰነቁ:: ራዕይ ያላቸው:: የሀገራቸውን ጥቅም በምንም አይነት ሁኔታ አሳልፈው የማይሰጡ:: እነኚህ ነገሮች ጸሎት ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ዘመቻም እንደሚያስፈልጋቸው አምናለሁ:: በርዕዮተ ዓለም እና በፖለቲካ እይታ የሚደረገው ውይይት እና ክርክር በይደር ትቶ መጀመሪያ ማህበራዊ ንቃተ ህሊናን ወደ መቀስቀሱ ዘመቻ መገባት አለበት ባይ ነኝ::
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Blog Archive
- April (18)
- May (8)
- June (2)
- July (1)
- October (2)
- December (7)
- March (1)
- July (1)
- August (1)
- January (5)
- February (3)
- March (2)
- June (2)
- April (3)
- May (3)
- August (2)
- September (1)
- October (3)
- November (4)
- December (4)
- January (4)
- February (3)
- March (8)
- April (2)
- May (2)
- June (1)
- December (2)
- January (2)
- February (1)
- May (2)
- July (4)
- September (1)
- October (2)
- November (1)
- September (1)
- December (1)
- December (1)
No comments:
Post a Comment